
የሕዝባችንን ኑሮ ለመቀየርና ሰላምን ለማስፈን ሌት ተቀን ያለ እረፍት እየሠሩ የነበሩት ጀግና ታታሪ ወንድማችን አቶ አህመድ አሊ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ በከሚሴ ከተማ ከሚገኘው መስጅድ ጁምአ ሶላት ሰግደው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የሠላም እና የአንድነት ፀር በሆኑ ፅንፈኞች በተተኮሰባቸው ጥይት በ39 ዓመታቸው መስዋዕት ሆነዋል፡፡
አቶ አህመድ አሊ ፅንፈኝነትን አምረው የሚታገሉ፣ በተሰማሩበት ሁሉ የሕዝብን ጥቅም የሚያስከብሩ ወንድማማችነትንና አብሮነትን ለማጠናከር ያለ እረፍት የሚሠሩ ታላቅ ሰው ነበሩ፡ፅንፈኝነት መሪዎችን በመግደል የሚያሸንፍ ቢመስልም የበለጠ ትግላችንን መራርና ፈጣን በማድረግ እንደ ብረት የሚያጠነክረን እንጅ ወደ ኋላ የሚመልሰን አይደለም፡፡
ፅንፈኝነት ሕዝብን ከሕዝብ ለማባላት ያገኘዉን አጋጣሚ ሁሉ ቢጠቀምም በሕዝባችን ትግልና አስተውሎት እንዲሁም እንደ ክቡር ወንድማችን አቶ አህመድ አሊ ባሉ ጀግኖች እየተቀበረ የመጨረሻውን የአልሞት ባይ ታጋይነት ተግባሩን ሲወተረተር ይታያል፡፡
ልበ ቅን መሪዎቻችንን ብናጣም የጀመሩትን ትግልና ትልም ከጫፍ ለማድረስ የበለጠ እንደ ብረት ጠንክረን የሕዝቦችንን አንድነት እናስቀጥላለን፡፡ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በብሔራዊ ገዥ ትርክት ላይ በማፅናት በየትኛዉም ቦታና ጊዜ ፅንፈኝነትን እንቀብረዋለን፡፡
“የወንድማችንን ነፍስ ፈጣሪ ይማርልን!”
ለወንድማችን አቶ አህመድ አሊ ወዳጅ ቤተሰቦችና ለትግል አጋሮቻቸው ሁሉ መፅናናትን እንመኛለን!!
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ባሕርዳር