
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የዘንድሮ ዓመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓት አስጀምረዋል።
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የዛምቢያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሮዝ ኬ ሳካላ “የምትተክል ሀገር፣ የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ መልዕክት በሚካሄደው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ላይ በመሳተፋቸው አመሥግነዋል፡፡
የዛምቢያ ሕዝብ እና መንግሥት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ዕውቅና ስለሰጡም ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ2011 ዓ.ም ከተወጠነበት ጊዜ አንስቶ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እንዳገኘ እና ለመጪው ትውልድ የሚጠቅም ትሩፋት ተደርጎ እንደተወሰደም ነው የተናገሩት።
አምባሳደር ሮዝ ኬ ሳካላ በዝግጅቱ ላይ በመገኘታቸው እና ኢትዮጵያውያን የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ግንባር ቀደም በመኾናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተከሰተው ድርቅ የአየር ንብረት ለውጥ ውጤት መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ይህንን ዓለም አቀፋዊ ፈተና ለመቅረፍ እርምጃ መውሰድ የሚገባው ጊዜ አሁን እንደኾነም ነው ያብራሩት።
መርሐ ግብሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በትብብር ያዘጋጁት ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በተጨማሪ ለቀጣይ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!