
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በንግግር እና በምክክር እንዲፈታ 15 አባላት ያሉት አመቻች የሰላም ካውንስል መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ ካውንስሉ ለየትኛውም ወገን ማዳላት ሳያሳይ በየትኛውም ወገን ጫና ሳይደረግበት ሁለቱም ወገኖች በቅንነት እንዲቀራረቡ እና እንዲደራደሩ የአመቻችነት ሚናውን ይወጣል። ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነትን እንደማያስተናግድም ገልጸዋል፡፡
የሰላም ካውንስሉ ለሁለቱም ወገኖች ባቀረበው ጥሪ የወገናችሁን ስቃይ ተረድታችሁ መሸናነፍ በማትችሉበት ጦርነት ከመቆየት ሁለታችሁም ማሸነፍ ወደ ምትችሉበት ንግግር እና ድርድር እንድትገቡ አመቻች የሰላም ካውንስሉ አበክሮ ይጠይቃል፣ ለማግባባትም ይጥራል ማለቱ ይታወሳል፡፡
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መንግሥት ሆደ ሰፊ ኾኖ ሰላም እንዲመጣ የራሱን ሚና ይጫዎት የሚል መልእክት ከሰላም ካውንስሉ እንደደረሰው ገልጸዋል። መንግሥት ለውይይት እና ለድርድር ራሱን በምን ያክል ደረጃ ያዘጋጃል የሚል ጥያቄ እንደቀረበላቸውም አንስተዋል፡፡
መንግሥት ለሰላም ዝግጁ መኾኑን ያስታወቁት ርእሰ መሥተዳድሩ አሁን ያለው ግጭት የአማራ ክልልን ሕዝብ እና የክልሉን አንድነት በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳው መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ችግር አለብን የሚሉ ወገኖች እና ጫካ ያሉ ወንድሞቻችን በውይይት ችግሮቻቸውን መፍታት አለባቸውም ብለዋል፡፡ እንደ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላም እንዲሰፍን እንፈልጋለን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሰላምን የሚያመጡ ማናቸውንም አካሄዶችን እና ዘዴዎችን ተከትለን እንሠራለን ነው ያሉት፡፡
በኅብረሰተብ ውስጥ ችግር እና ጥያቄ ሊኖር ይችላል፤ የችግር መፍቻ መንገዱ ግን ግጭትና ነውጥ መኾን የለበትም ብለዋል፡፡
አሉ በሚባሉ ችግሮች በመንስኤያቸው ዙሪያ እና በሚፈቱበት መንገድ መነጋገር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት የሰላም ምክር ቤቱ ለሚያቀርበው ማናቸውም ጥሪ ዝግጁ ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡
የክልሉ መንግሥት ለመወያየትም፣ ለመደራደርም ዝግጁ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት በየትኛውም ቦታ፣ በየትኛውም አማራጭ በማንም ሰው ለመደራደር እና ለመወያየት ፍላጎት አለው ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ ሰላም እንዲያገኝ እንፈልጋለን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ አንድነት እንዲጠናከር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ አሁን አሁን የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ ቢመጣም ሰዎች እንደፈለጉት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ የለም፣ አሁንም ትንንሽ ችግሮች በየአካባቢው እየተከሰቱ ነው፣ ችግሮች አስከፊ ጉዳት እንዳያደርሱ መወያየት እና መደራደር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
“አሁን ያለው ሁኔታ ተሻሽሏል ብለን ድርድርን ከንቱ ልናደርገው አንችልም” ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ፡፡
ለታጠቁ ኃይሎች የምናስተላልፈው መልእክት አሁን ያለው ግጭት የመጨረሻው መቋጫው ውይይት እና ድርድር መኾኑን ነው፣ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ውይይት መጥተን እጃችንን መጨባበጣችን አይቀርም ብለዋል፡፡ መወያየት ላይቀር ሕዝብ መጎዳት እና የክልሉ ሀብት መውደም የለበትም ሲሉ የውይይት እና የምክክርን ተገቢነት አስረድተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!