
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የጤና ባለሙያዎችን እያፈራ የሚገኝ ተቋም ነው። ኮሌጁ በ2016 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን እና በቀጣይ ለመሥራት ባቀዳቸው ሥራዎች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዘመነ ሀብቱ ኮሌጁ ባለፋት ጊዚያት በትምህርት ጥራት፣ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና በመስጠት፣ ችግር ፈች የምርምር ሥራዎችን በመሥራት፣ የማኀበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በማከናወን እና በሌሎች በርካታ መስኮች ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
ተማሪዎች በሥልጠና ወቅት የተግባር ልምምዳቸውን በተገቢው መንገድ እንዲከታተሉ በማድረግ እና አቅማቸውን እንዲያሣድጉ በማድረግ በኩል ኮሌጁ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ጤና ሳይንስ ኮሌጁ ለልህቀት ተግቶ እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ዘመነ ሀብቱ በ2017 ዓ.ም የዲግሪ ፕሮግራሞችን ለመጀመር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የደብረ ታቦር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ብርሃን ሙሉ በበኩላቸው የጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ችግሮችን ተቋቁሞ የጤና አገልግሎት ሥርዓቱ እንዲጠናከር እየሠራ ያለው ሥራ አበረታች መኾኑን ገልጸዋል። ጤናማ እና አምራች ማኀበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ እንደኾነ በምክክር መድረኩ ተነስቷል።
በመድረኩ የተገኙት ባለድርሻ አካላት ለኮሌጁ ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!