ለ2016 ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ተፈታኝ ተማሪዎች ተናገሩ።

15

ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመምህራኖቻቸው እና በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህራን ሲታገዙ መቆየታቸውን እና በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተፈታኝ ተማሪዎች ተናግረዋል። ከፈተናው ጥሩ ውጤት እንደሚጠብቁም ነግረውናል፡፡ ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ በተለያየ አግባብ ሲያግዟቸው መቆየታቸውንም መምህራን እና የትምህርት ባለሙያዎች ገልፀዋል፡፡

የዘንድሮው ዓመት ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከሐምሌ 03 እስከ ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም ይሰጣል። ተማሪ ሙላቴ ማራለም እና ማህደር ምክር እንዳሉት በክፍል ሲሰጣቸው የቆየውን ትምህርት በአግባቡ ሲከታተሉ በመቆየታቸው፣ ቤተ መጽሐፍ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ የ24 ሰዓት አገልግሎት በማግኘታቸው፣ በተመረጡ መምህራኖቻቸው እና በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት እና ሞዴል ፈተናዎችን ወስደዋል።

በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከሚገኙት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል የዳግማዊ ቴዎድሮስ መሰናዶ ትምህርት ቤት የሒሳብ መምህር ደስአለው ዓለም በሰጡን አስተያየት የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ለማዘጋጀት ሲሰሩ ቆይተዋል። በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የዳግማዊ ቴዎድሮስ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህርት ሜሮን ፀጋ እንዳሉት ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና የሚፈተኑ ተማሪዎችን ለማብቃት እና ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሢሠራ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በክፍል ውስጥ የነበረው መማር ማስተማር በጥሩ መንገድ ሲሰጥ መቆየቱን፣ በተመረጡ የትምህርት ቤቱ መምህራን እና በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱን አንስተዋል። የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እየበሩ አዕምሮ እንዳሉት በ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎችን ለፈተናው ለማዘጋጀት እና ብቁ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሢሠሩ ቆይተዋል ብለዋል። ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎንም ተማሪዎችን በሥነ ልቦና የማዘጋጀት ሥራ ሲሰራ ቆይቷል ነው ያሉት።

በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር 1 ሺህ 823 ተማሪዎችን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ላይ እንደሚያስፈትን ከከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ600 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ሥራዎች እንደሚሳተፉ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።
Next articleየጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ2017 የዲግሪ ፕሮግራሞችን ለመጀመር እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ።