
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አቶ ፈንቴ አጥናው በመሬት ጥበት እና መደኽየት በሚቸገር ማኅበረሰብ ውስጥ ይኖራሉ። ትዳርን ለመምራት፣ ልጅ ወልዶ ለማሳደግ፣ አሳድጎ ለቁም ነገር ለማብቃት፣ ዘርን ተክቶ ትውልድ ለማስቀጠል እና ችግርን ለማስወገድ ከማኅበረሰቡ ጋር ይመካከራሉ።
የመሬት ጥበት፣ የአፈር መሸርሸር፣ የእንስሳት ቀለብ ችግር የእነ አቶ ፈንቴ ቀበሌ የግብርናው ዘርፍ ማነቆዎች ናቸው። በየዓመቱ በበጋ እርከን በክረምት ችግኝ ቢተከልም ጠብ የሚል ነገር አልታየም። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣው የደን መጥፋት እና የምርታማነት መቀነስም ሀገሬውን አሳስቦታል።
እነ አቶ ፈንቴ ግን ተስፋ ባለመቁረጥ ችግኝ ከመትከል አልቦዘኑም። የግብርና ባለሙያዎች ውትወታም ልማቱን አላስረሳቸውም። በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ደን ልማት ዘመቻ ታወጀ። ሰኔ እና ሰኞ ተገናኙ እና እነ አቶ ፈንቴ መከሩ፤ ዘከሩ – ‘እስኪ እስካሁን ያልሞከርነውን እንሞክር’ ብለው ተነሱ። አቶ ፈንቴም ለተፋሰስ ልማት አስተባባሪነት ተመርጠው የሕዝቡን ምክር ሊተገብሩ ኀላፊነትን ተቀበሉ።
በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ የጎሃ ቀበሌ ነዋሪዎች ጉልበታችን፣ ገንዘባችን፣ መሬታችን ካባከንን አይቀር ለምን አንጠቀምም? የሚል የብልህ ሰው ሃሳብም ያመነጨው የእነ አቶ ፈንቴ የተፋሰስ ልማት ኮሚቴ ሁልጊዜ ከመልፋት ለተወሰነ ጊዜ ታግሶ ደንን ማልማት እና መጠቀምን በመፍትሄነት ተስማምቶ ኅብረተሰቡን በማስተባበር በተፋሰስ የደን ልማቱን በአዲስ ወኔ እና ተስፋ እያስኬዱት ነው።
አቶ ፈንቴ አሁን ላይ የቁጥር አንድ ተፋሰስ ልማት ኮሚቴ ሠብሣቢ ናቸው። የአረንጓዴ አሻራ ደን ልማት ሲጀመር በ20 ሄክታር ተፋሰስ ላይ ከአካባቢያቸው ነዋሪ ጋር የማኅበረሰብ ደን አልምተዋል። በየዓመቱም እያሰፉት ሲኾን ደኑ በሚቀጥለው ዓመት ለጥቅም ይደርሳል ብለው ተስፋ አድርገዋል።
በተፋሰስ ደን ልማቱ 90 የቤተሰብ ኀላፊዎች የወል የባለቤትነት ደብተር የያዙበት ሲኾን ባቋቋሙት ኮሚቴ አማካይነትም ይጠብቁታል፤ ያሥተዳድሩታል። ኅብረተሰቡ የመረጣቸው ሰዎች ሳሩን እያጨዱ እንዲጠቀሙ እና ደኑን እንዲጠብቁ አድርገዋል። ስለ ተፋሰሱ በየጊዜው እየተወያዩ አጥፊዎችን እየገሰጹ እንዳለሙት ነው አቶ ተስፌ የገለጹት።
”ለምነቱን አጥቶ የነበረ መሬት ዛሬ ላይ አገግሞ እና ለምቶ በጎርፍ የተሸረሸረ እና የተበላ መሬት መኾኑ አይታወቅም” ያሉት አቶ ፈንቴ በየዓመቱ እያሰፉት እንደኾነም ተናግረዋል። የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎችን በማሳደግ ተፋሰሱን አልምተን አድነነዋል፤ ለጊዜው ሳር በማጨድ ከውጤቱ እየተቋደስን ሲኾን ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮም ዛፉ ይደርስልናል ነው ያሉት። በአዋሳኝ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮችም ልማቱን አይተው በመማር በግል ማሳቸው ላይ የአፈር መጠበቂያ እና እንደ ጌሾ ያሉ የገበያ ተክሎችን ተክለው እየተጠቀሙ ነው ብለዋል።
እነ አቶ ተስፌ ዘንድሮም በበጋው ያዘጋጁትን ሰባት ሄክታር መሬት ለመትከል ተዘጋጅተዋል። የተፋሰሱ መሪዎች በራሳቸው ወጪ ችግኞችን ወደ ተፋሰሱ በትራክተር መውሰድም ጀምረዋል። በደቡብ ጎንደር ዞን የደራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ ታደሰ ገብረኪሮስ በወረዳው ባለፉት የአረንጓዴ አሻራ የተከላ ዓመታት 8 ነጥብ 95 ሚሊዮን ችግኝ በ17 ሺህ 135 ሄክታር መሬት ላይ መተከሉን እና የጽድቀት መጠኑም በአማካይ 74 ነጥብ 5 በመቶ መኾኑን ገልጸዋል። ከወረዳው ስፋት 11 ነጥብ 5 በመቶ ይሸፍናልም ብለዋል።
በወረዳው 256 ተፋሰሶች ሁለንተናዊ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እየተሠራባቸው ሲኾን በእያንዳንዱ ቀበሌም አንድ ሞዴል ተፋሰስ አለ። ዘንድሮ 18 ሚሊዮን ችግኝ በ2 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ቡድን መሪው ጠቅሰዋል። ወረዳቸው የተሻለ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ያለው መኾኑን የጠቀሱት አቶ ታደሰ ልማቱን ዘላቂ እና ጠቃሚ እንዲኾን ኅብረተሰቡን በማወያየት ለማሳመን ከልብ እንሠራለን ነው ያሉት። በወረዳው ሰብልም ኾነ የእንስሳት ልማት ያለ ተፈጥሮ ሃብት ውጤታማ እንደማይኮን በእምነት ተይዞ በቅንጅት እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል፡፡ በዚህም ውጤታማ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ያደጉ ሀገራትን የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሕግን በምሳሌነት የጠቀሱት ቡድን መሪው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ውጤታማ እና ዘላቂ እንዲኾን የአካባቢ ጥበቃ፣ የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሕጉን መተግበርም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የደን ባለሙያ ወይዘሮ ባንችአምላክ ሞላ የአረንጓዴ አሻራ 5ኛ ዓመት ተከላን ለመፈጸም ክልላዊ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል። በዘንድሮው ተከላ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኝ በ170 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል 750 ሚሊዮን ጉድጓድ መዘጋጀቱንም ነው የነገሩን።
ባለፉት ዓመታት የተተከለው ችግኝ የጽድቀት መጠን አበረታች መኾኑን የተናገሩት ወይዘሮ ባንችአምላክ ዘንድሮም የጽድቀት መጠን እንዲጨምር፦
👉 በቅድመ ተከላ – ኅብረተሰቡን ማወያየት፣ የተከላ ቦታ እና የችግኝ ዝርያ መረጣ፣ የጉድጓድ ዝግጅት
👉 በተከላ ጊዜ – በማጓጓዝ እና የተከላ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ
👉 ከተከላ በኋላ – አረም፣ ኩትኳቶ እና ጥበቃ በትኩረት እየተሠሩ ነው ብለዋል።
የጽድቀት መጠኑ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ እንደኾነ የተናገሩት ወይዘሮ ባንችአምላክ በቀጣይ ያለመጽደቅ ችግርን ለመቀነስ አስፈላጊው ማስተካከያ እንደሚደረግ ገልጸዋል። የወል መሬቶችን ማኅበረሰቡ የባለቤትነት ደብተር ይዞ እንዲያለማቸው በውጤታቸውም ተጠቃሚ እንዲኾን እየተሠራ ነው ብለዋል። የተፋሰስ ኮሚቴም ልማቱን እንዲያስተባብር ማድረግ የበለጠ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።
ሰሜን ሸዋ ዞን፣ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ደቡብ ጎንደር እና ሰሜን ጎጃም ዞን የተፋሰስ ደን ልማትን አጠናክረው በመሥራት ተጠቃሽ እንደኾኑ ባለሙያዋ ጠቅሰዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ ባለፉት 5 ዓመታት 7 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን፣ 79 ነጥብ 6 በመቶ አማካይ የጽድቀት መጠን እንደተገኘ እና የክልሉ የደን ሽፋንም ወደ 16 ነጥብ 3 በመቶ ማደጉን ጠቅሰዋል።
በውጤቱም የታችኛው ተፋሰሶች ውኃ ማመንጨታቸውን፣ የአፈር ለምነት መሻሻሉን፣ የእንስሳት መኖ ልማት መጨመሩን፣ ለግብርና ልማት ምቹ ሥነ ምሕዳር መፈጠሩን ተናግረዋል። ዘንድሮም ተፋሰሶች ለምተው ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲኾን ከተከላ በኋላ ችግኞችን መንከባከብ እና ተፋሰሶችን መጠበቅ በትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል። የጸጥታ ችግር ቢኖርም ልማት ስለማይቋረጥ ችግሩን ከመፍታት ጎን ለጎን መንግሥት ልማቱ እንዲቀጥል ለሚያደርገው ጥረት ሁሉም በቅንጅት ለመሥራት ሊተባበር እንደሚገባ ነው ዶክተር ድረስ ያሳሰቡት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!