ባለፉት ወራት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የወባ በሽታ ሕሙማን መመዝገቡ ተገለጸ።

43

ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ሥርጭት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል። በአማራ ክልል ከሚኖረው ሕዝብ 85 በመቶ የሚኾነው ለወባ በሽታ ተጋላጭ እንደኾነ መረጃዎች ያሳያሉ። ባለፉት ወራት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የወባ በሽታ ሕሙማን መመዝገቡም ተጠቁሟል።

በክልሉ 34 ወረዳዎች ደግሞ የክልሉን የወባ ሥርጭት 70 በመቶ ይሸፍናሉ። ከእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ደራ እና ቋራ ወረዳዎች ይገኙበታል። የደራ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ሲስተር ሙሉ ያለው እንዳሉት የወባ በሽታ ባለፈው ዓመት ከነበረው በእጥፍ ጨምሯል። የፀጥታ ችግሩ የቁጥጥር ሥራ ለመሥራት እና ግብዓት በወቅቱ ለማቅረብ አለማስቻሉንም አንስተዋል። እስከ አሁን ርጭት እንኳ አለመካሄዱን ነው ያነሱት። ከ100 ሺህ በላይ ሕሙማን መመዝገቡንም ገልጸዋል።

የቋራ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ ቀጠለ ፋሲል እንዳሉት በወረዳው የወባ ታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። በሽታው የወረዳው ዋነኛ ችግር መኾኑንም ነው የገለጹት። በሳምንት እስከ 900 ሕሙማን እንደሚመዘገቡም አብራርተዋል።

ባለሙያው እንዳሉት በፀጥታ ችግር የወባ መድኃኒት እና ሌሎች ግብዓቶችን ማቅረብ አልተቻለም፤ ርጭትም አልተከናወነም። ወረዳው የኢንቨስትመንት መዳረሻ በመኾኑ በርካታ የቀን ሠራተኞችን እንደሚያስተናግድ ገልጸዋል። መንግሥት ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል። የአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት አሁን ላይ ክልሉ በተለያዩ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች እየተፈተነ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የወባ በሽታ አንዱ ነው።

በተለይም ደግሞ በተያዘው በጀት ዓመት የወባ ሥርጭቱ በክልሉ መጨመሩን ገልጸዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የርጭት እና የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የኅብረተሰብ ጤና ጉዳይ ለአንድ አካል የሚተው ጉዳይ አለመኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ የክረምቱን መግባት ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ በሽታ ለመከላከል ተቋማት፣ አጋር ድርጅቶች እና ማኅበረሰቡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የወባ ሥርጭት ባለባቸው 222 ወረዳዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው። እነዚህ ወረዳዎች የሀገሪቱን የወባ ሥርጭት 76 በመቶ ይሸፍናሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በአማራ ክልል 34 ወረዳዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

በቀጣይ ስድስት ወራት ከፍተኛ የወባ ሥርጭት ባለባቸው በእነዚህ ወረዳዎች ያለውን የወባ በሽታ 50 በመቶ ለመቀነስ ትኩረት ተደርጓል። ለዚህ ደግሞ ከመድኃኒት አቅራቢ ኤጄንሲ፣ ከመድኃኒት ቁጥጥር ኤጄንሲ፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ ነው።
በቀጣይ ወራትም ቁጥጥር ላይ ትኩረት እንዲደረግ አሳስበዋል። በፌዴራል ደረጃ የርጭት ኬሚካል ግዥ ሂደት ላይ መኾኑንም ገልጸዋል።

የተሰራጨውን አጎበር ለተቀመጠለት ዓላማ እንዲውል ክትትል ማድረግ ይገባል ብለዋል። ተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግም ነው የገለጹት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለ900 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ገለጸ።
Next article“ለምን አንጠቀምም” አርሶ አደሮች