
ደሴ: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደሴ ከተማ ለሥራ ፈላጊዎች የመስሪያ ቦታ ለማስረከብ ዓላማ ያደረገ ውይይት እየተካሄደ ነው።
የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው በከተማዋ በ2016 በጀት ዓመት ለ27 ሺህ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱን ገልጸዋል። ባለፉት 11 ወራትም ለ22 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አንስተዋል። በከተማዋ የተለያዩ የልማት ሥራዎች መከናወናቸው ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ከሰኔ 29/2016 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ ለተመረጡ 2 ሺህ 600 ሥራ ፈላጊዎችም የመስሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት ለማስረከብ ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል። በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) በበጀት ዓመቱ ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በማቀድ እስካሁን 900 ሺህ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
በክልሉ የተፈጠረው ሁኔታ ለሥራው ፈታኝ ቢኾንም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ በተሰጠው ትኩረት ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል። ሥራ ከመፍጠር ባለፈ ውጤታማ እንዲኾኑ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ እየተደረገ ስለመኾኑ ኀላፊው አስረድተዋል።
ዘጋቢ:- ተመስገን አሰፋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!