
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከ36 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ለመሥራት ማቀዱን የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ አስታውቋል፡፡
በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በየዓመቱ እየተጠናከረ የመጣ ሲኾን በተያዘው የክረምት ወራትም በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ ስለመኾኑ ነው የተገለጸው፡፡ በተያዘው ክረምት ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማኅበረሰቡን እና ከተማዋን የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለመሥራት መዘጋጀታቸውን በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የሚሳተፉ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡
ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ መካከል አስተያየታቸውን የሰጡን ወጣት ማዛሽ ኃይሉ እና ዘካሪያስ ደጀኔ ለብዙ ዓመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ በባለፈው ዓመትም በበጎ-ፈቃድ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መሥራታቸውን ነው ያስረዱት፡፡ በዚህ ዓመት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም ማኅበረሰባቸውን እና ከተማቸውን የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከበጎ ፈቃድ ተግባራቸው ጎን ለጎን ሰላም እና ፀጥታን ለማስፈን ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡ የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ እሸቱ ውለታው በባለፈው ዓመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መሠራታቸውን አውስተዋል፡፡ ኀላፊው በዚህ ዓመትም በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ36 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ሥራዎችን ለመሥራት ታቅዶ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በአረንጓዴ ልማት፣ በከተማ ጽዳት እና ውበት፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን፣ አልባሳትን ለአቅመ ደካሞች በማሠባሠብ፣ በችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖች እርዳታ በማሠባሠብ እና ሌሎችም ሥራዎች ወጣቶቹ እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት፡፡ በተያዘው የክረምት ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከእስካሁኑ በበለጠ አግባብ ለማስኬድ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በጥሩ መነሳሳት እና ወኔ ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው እና ማኅበረሰቡም በጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ባለው አቅም ማገዝ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደበበ አክሎግ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማኅበረሰቡን እና ከተመዋን የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለመሥራት መተጋገዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
እንደ ደብረታቦር ከተማ በበጎ ተግባር እንቅስቃሴ መከናወን የሚገባቸው በርካታ ተግባራት መኖራቸውን ያነሱት አቶ ደበበ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው የተናገሩት። የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን ለብዙ ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለያዩ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን አውስተው በዚህ ዓመት የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም ማኅበረሰቡን እና ከተማዋን የሚጠቅሙ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ውጤታማ በኾነ አግባብ ማስኬድ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በከተማ አሥተዳደሩ ብሎም በክልሉ ሰላም እና ፀጥታን ለማስፈን ብሎም በዘላቂነት ለማስጠበቅ ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም ከንቲባው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት ከባለድርሻ አካላት ጋር የ2016 ዓ.ም የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ እንደሚገኝ ከደብረታቦር ከተማ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!