በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቀጣይ በሚከናወነው የሰላም ኮንፈረንስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ዙሪያ ምክክር እየተካሄደ ነው፡፡

13

ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)“ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ቀጣይ በሚከናወነው የሰላም ኮንፈረንስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ዙሪያ ምክክር እየተካሄደ ነው፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያምን ጨምሮ ሌሎች የዞን እና የወረዳ መሪዎች ተገኝተዋል። በዞኑ የሚታዩ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በዚህ ኮንፈረንስ የጋራ መተማመን ለመፍጠር የሚያስችል ጥልቅ ምክክር ማድረግ እንደሚገባ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያም ተናግረዋል።

ዋና አሥተዳዳሪው የገጠመውን ችግር ለመሻገር ሁሉንም የሚያስማማ ወጥ የኾነ የትግል ስልት መያዝ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ የዞኑ ሕዝብ በፓለቲካው፣ በኢኮኖሚው በልማቱ እና በሰላሙ ተጠቃሚ የሚኾንበት አቅጣጫ በማስቀመጥ ሕዝቡን ማሻገር ይገባልም ብለዋል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈንታሁን ስጦታው በኮንፈረንሱ ድክመቶችን ማረም እና ማስተካከል የሚያስችል ውስጣዊ አንድነት መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የተጀመረውን የሰላም ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት እና የልማት ሥራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ በማሻገር የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባም አብራርተዋል። በኮንፈረንሱ አስፈላጊነት እና ዓላማ ዙሪያ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ካሳሁን ንጉሴ ናቸው፡፡
ቀጣይ በሚከናወነው የሕዝብ የሰላም ኮንፈረንስ በወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ የሚመከር ውይይት ከወረዳ እስከ ቀበሌ እንደሚካሄድ ነው በሰነዳቸው ያስገነዘቡት።

ኮንፈረንሱ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የሚካሄድ ሲኾን የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ምሁራን እና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊዎች እንደሚኾኑ ከዞኑ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት እና በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
Next article“የፀጥታ ኀይሉን በአመለካከት፣ በሥነ ልቦና እና በተግባር ለማብቃት የተጀመሩ ሥልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ” የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር