
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የግብርናውን ዘርፍ ምርታማ ለማድረግ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የአፈር ለምነትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡
በተለይም መጠቀም ከሚገባው ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ጎን ለጎን የኮምፖስት ዝግጅት እና አጠቃቀምን ተግባራዊ ማድረግ ዘላቂ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ እና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው ያስገነዘበው፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ማዘጋጀት እንደሚቻል የገለጸው ሚኒስቴሩ አሁን ላይ በአርሶ አደሩ የተለመዱ ዋነኛ አሠራሮች ከመሬት በላይ እና በታች የማዘጋጀት ዘዴዎች ስለመኾናቸው ገልጿል፡፡
የአየር ንብረታቸው ቀዝቃዛ በኾኑ አካባቢዎች ኮምፖስቱን ለሚያዘጋጁ ደቂቅ ህዋሳት ሙቀት ለመስጠት እና የመብላላቱን ሂደት ለማፋጠን ሲባል በጉድጓድ ውስጥ እንዲዘጋጅ እንደሚደረግ ነው የተብራራው፡፡ በሞቃታማው አካባቢ ደግሞ ከመሬት በላይ ግብዓቶችን በመከመር እንደሚዘጋጅ ነው ያስገነዘበው፡፡
ሚኒስቴሩ ኮምፖስት በሚዘጋጅበት ወቅት መካተት የሌለባቸው ግብዓቶችን ሲገልጽ፡-
✍️ዘር ያፈሩ የአረም ተክሎች
✍️የባህር ዛፍ የቅጠል ርጋፊዎች፣
✍️የተለያዩ ቀለማትን የያዙ ወረቀቶች
✍️የከሰል አመድ
✍️በበሽታ የተጠቁ እጽዋቶች
✍️የማይበሰብሱ ልዩ ልዩ ቁሶች
✍️የብረት ነክ ቁሶች፣ የነዳጅ ውጤቶች፣ ስጋ እና የስጋ ውጤቶች
✍️አጥንት፣ ስብ፣ ማናቸውም የአሳ ግልፋፊዎች፣ የወተት ተዋጽአዎች እና መሰል
✍️ሥጋ በል የቤት እንስሳት ኩስ
✍️ሰው ሠራሽ ኬሚካሎች (ጸረ- አረም እና ጸረ ተባይ) መካተት እንደሌለባቸው ያስታወሰው ሚኒስቴሩ አርሶ እና አርብቶ አደሩ የቀረቡትን ምክረ ሃሳቦች መሠረት በማድረግ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀት የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባው መግለጹን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!