
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 29ኛ መደበኛ ጉባኤውን በእንጅባራ ከተማ እያካሄደ ነው።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሙሉዓዳም እጅጉ በጉባኤው መክፈቻ ላይ “ካሉብን ውሥብሥብ ችግሮች በድል ለመሻገር በችግሮቻችን ምልከታ ላይ የጋራ አረዳድ መያዝ እና በመውጫ መንገዶች ላይ መተባበር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው” ብለዋል። አያት ቅድመ አያቶች የትኛውንም አይነት ሕዝባዊ እና የልማት ድሎችን በስኬት የተወጡት በተበተነ ኀይል ሳይኾን በጠንካራ አንድነት እንደኾነ ታሪክ ምስክር ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ምርት እና ምርታማነትን መጨመር፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ አሠራሮችን መዘርጋት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መፍታት ቀጣይ በትኩረት መፈጸም የሚገባቸው ጉዳዮች መኾናቸውንም አፈ ጉባኤዋ አንስተዋል። ምክር ቤቱ በአንድ ቀን ውሎው የግብርና፣ የትምህርት፣ የሰላም እና ፀጥታ መምሪያዎችን ሪፖርት እያዳመጠ ሲኾን የተለያዩ አስፈጻሚዎችን ሹመት መርምሮ በማጽደቅ እንደሚጠናቀቅም ከወጣው መርሐ ግብር ለመረዳት ተችሏል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!