
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ተማሪ ፍቅር አዲስ በደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ የመቅደላ ወረዳ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪ ናት፡፡ ተማሪ ፍቅር አዲስ ከአሚኮ ጋር በነበራት ቆይታ እንዳለችው ሁሌም የምታልመው በውጤቷ ቤተሰብንም ሀገርንም ለማኩራት ነው፡፡
ይህን ሕልም ለማሳካት ጠንክራ ሥትሠራ መቆየቷን የተናገረችው ተማሪዋ የጸጥታ ችግሩ የሥነ ልቦና ጫና ቢያሳድርም ችግሩን ተቋቁሞ ሕልምን ለማሳካት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጓን ነው የገለጸችው፡፡ ለፈተናው በቂ ዝግጅት እንዳደረገች እና መምህራን የትርፍ ጊዜ ትምህርት በመስጠት ያግዟቸው እንደነበርም ነው ያስረዳችው፡፡
ቤተሰቦቿ የተሻለ ውጤት እንድታስመዘግብ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ በመኾኑ ይህን ታሳቢ አድርጋ መዘጋጀቷን ነግራናለች። የቤተሰብ እና የትምህርት ቤቷን ስም ከፍ ለማድረግ ታሳቢ አድርጋ እንደተዘጋጀችም ገልጻለች፡፡ ተማሪ አብርሃም አገዘ የደላንታ ወረዳ ወገል ጤና አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪ ነው፡፡
ተማሪው ከቤተሰብ ባለፈ ትምህርት ቤቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስሙ ክፍ ብሎ እንዲጠራ ለማድረግ የሚያስችል ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት ማድረጉን ነው የተናገረው፡፡ የትምህርት ዓመቱ የጸጥታ ችግር የነበረበት እና በሥነ ልቦናም የሚጎዳ ቢኾንም ትምህርት ቤትን እና ክልልን ሊያሰጠራ የሚችል ሥራ መሥራት አስፈላጊ እንደኾነ በማመን ችግሮችን ተቋቁመው ዝግጅት ስለማድረጋቸው ነው ያስረዳው፡፡
መምህራንም ለፈተናው ትኩረት ሰጥተው በተቃራኒ ፈረቃ የማካካሻ ትምህርት ያስተምሯቸው እንደነበር እና በቤተ መጽሐፍ እስከ ምሽት 12 ሰዓት እንዲጠቀሙ ስለመፈቀዱ ነው የገለጸው፡፡ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ዝግጅት አስመልክቶ የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ዓለምነው አበራ እንዳሉት በደቡብ ወሎ ዞን በ58 ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ይሰጣል፡፡
ኀላፊው በዞኑ 6 ሺህ 741 የማኅበራዊ ሳይንስ እና 5 ሺህ 518 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በአጠቃላይ 12 ሺህ 259 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ በአንዳንድ ወረዳዎች የጸጥታ ችግር ቢኖርም ተማሪዎች በጸጥታ ኀይሉ እገዛ እና ክትትል ፈተናውን እንደሚወስዱ ነው ያብራሩት፡፡ ሁሉም ተማሪዎች በወረቀት እንደሚፈተኑም ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎችን የማዘጋጀቱ ሥራ በሚገባ የተሠራ በመኾኑ ያለምንም ችግር ፈተናውን እንደሚወስዱ ያላቸውን ዕምነት ተናግረዋል፡፡ የ12ኛ ክፍል ፈተና ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ ከትምህርት ሚኒስቴር የወጣው የፈተና የጊዜ ሰሌዳ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!