
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 36ኛ መደበኛ ጉባኤ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን አጽድቋል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጀውን ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
አዋጁ ቁጠባን እና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ትልቅ ሚና ያለው እና የካፒታል ዕቃዎችን ሳይጨምር በዕቃ እና አገልግሎት ፍጆታ ላይ የተጣለ ስለመኾኑ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ አዋጁ በታክስ ከፋዩ እና በታክስ ሰብሳቢው መስሪያ ቤት መካከል ሲፈጠር የነበረውን አለመግባባት በማስወገድ ምቹ የኾነ የታክስ አስተዳደር እንዲኖር የሚያግዝ እንደኾነም ተመላክቷል፡፡
መንግሥት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሃብት ተገቢውን ድርሻ እንዲያገኝ የሚያስችል እና ከታክስ ነፃ መብት ገደብ የሚያበጅ አዋጅ እንደኾነ አቶ ደሳለኝ ባቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ አስረድተዋል፡፡ ምክር ቤቱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማፅደቁን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!