
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ጋር በጋራ የምትሠራ ሀገር መኾኗን እና የሚነሱ ችግሮችንም በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሥትሠራ መቆየቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት ከሕወሐት ጋር ጦርነት ላይ በነበረበት ወቅት “አወዛጋቢ” የተባሉ የሁለቱ ሀገራት የድንበር አካባቢ ሱዳን ይዛ እንደነበር አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የሱዳንን ግጭት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወደ እርምጃ አለመግባቱን በማሳያነት ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ በግጭቱ ምክንያት ለሁለት ዓመት ያልተከፈለ የኤሌክትሪክ ክፍያ ቢኖርም አገልግሎቱ አለመቋረጡ መንግሥት ለዲፕሎማሲ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱ ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ሁለቱ ተፋላሚ ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ መንግሥት እንደሚሠራም ነው የተናገሩት፡፡ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ሕዝብም ወንድማማች መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሕዝብ እና መንግሥት አንድነት ሥትሠራ መቆየቷን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ ዋጋ መከፈሉንም አንስተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!