“አቅማችን በፈቀደ መጠን እየተከታተልን ሌቦች ላይ እርምጃ መውሰድ አለብን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

19

ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም ሙስና ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምልከታ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ ሌብነት ነቀርሳ ነው፣ ሌባ ሰው ምንም ቢኾን ዋጋ የለውም፣ ሌብነት ትንሹም ኾነ ትልቁ መጥፎ ነው መጥፋት አለበት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሌብነት ልንዋጋው ይገባል ብለዋል፡፡

ይህ ምክር ቤት ሙስናን እንድንታገል ይፈልጋል ወይ? የኢትዮጵያ ሕዝብስ ሙስናን እንድንታገል ይፈልጋል ወይ? ብለው የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌቦችን ለመቆጣጠር ሕግ ስናወጣ ጤነኞችን ለመንካት ነው ተብለናል ነው ያሉት፡፡

ሙስናን ለመዋጋት የተቋቋመው ኮሚቴ ብዙ ሥራ ሠርቷል፤ ነገር ግን በቂ አይደለም፤ ሙስናን ለመታገል ከዚህ በላይ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡ “መቶ በመቶ ማረጋገጥ እችላለሁ በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ መንግሥታዊ ሌብነት የለም፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንዘርፍም፣ ያገኘናትን ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ፈሰስ እናደርጋለን” ነው ያሉት፡፡

ነገር ግን ግለሰቦች አይሰርቁም ማለት ግን አይደለም ብለዋል፡፡ ጥርጣሬ ሲኖር እንደሚያጣሩ እና ክትትል እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡ “አቅማችን በፈቀደ መጠን እየተከታተልን ሌቦች ላይ እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ሌብነት ለኢትዮጵያ አደገኛ ጸር መኾኑን ማስተማር አለብን፣ ለሌብነት እንዳይመች አሠራሮችን መቀየር አለብን” ነው ያሉት፡፡

ሙስናን ለመዋጋት ከ600 በላይ አሠራሮችን ማሻሻላቸውንም አመላክተዋል፡፡ ሌብነቱን እናስቀር እንታገል፣ ሌብነቱን ማጋነንም ተገቢ አይደለም ነው ያሉት፡፡ የፕሮጀክት ሥራዎች ክትትል እየተደረገባቸው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የኮሪደር ልማት እንደ ሀገር ትልቅ ሥራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የኮሪደር ልማት በሁሉም ቦታ እንዲለመድ ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የፕሪቶሪያው ስምምነት በዋናነት በትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር እንዲቋቋም እና አገልግሎት እንዲቀጥል ማድረግ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን እያስመረቀ ነው፡፡