
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ሥብሠባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት ተከትሎ የመጣው የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸሙ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ረገድ የባሕል ለውጥ ያመጣንበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የፕሪቶሪያው ስምምነት በዋናነት በትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር እንዲቋቋም እና አገልግሎት እንዲቀጥል ማድረግ ነው” ብለዋል፡፡ ተኩስን በማቆም አገልግሎትን በማስጀመር ትልቅ ድል አግኝተንበታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባንኮች፣ አየር መንግድ፣ ቴሌኮምን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶች ወደ ሥራ ገብተዋል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ የመጣው ለውጥ መልካም መኾኑን እና መንግሥት ስምምነቱን በቁርጠኝነት ለመፈጸም እየሠራ ስለመኾኑም አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ከትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር ውጭ ያሉ እና አሁንም ካለፈው እልካቸው እና ችግራቸው ያልተላቀቁ ግለሰቦች የሚፈጥሩት ችግር እንዳለም ጠቁመዋል፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት በዋናነት በትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር ማቋቋም እና አገልግሎት ማስጀመር ቢኾንም ከዚያ የተሻገረ ሥራ ተሠርቷልም ነው ያሉት፡፡ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ሂደት ክፍተቶች ቢኖሩበትም መንግሥት በሆደ ሰፊነት እና አስተዋይነት ችግሮችን እያረመ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!