ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁዎች ነን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

33

ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከሰላም ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሰዎች የታገሉት የሥልጣን መቀያየር ለማድረግ ሳይኾን ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት መኾኑን ገልጸዋል። አዲስ ሀሳብ፣ አዲስ አካሄድ ያስፈልጋል በሚል ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

የለውጡ አንኳር ጥያቄዎች በሁለት ይከፈላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያው ነባር ችግሮች ናቸው። ከጥንት የመጡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ታሪካዊ ነባር ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ወቅታዊ ችግሮች ናቸው ነው ያሉት። ከወቅታዊ ችግሮች መካከል ምጣኔ ሃብታዊ ስብራት አንዱ ነው። እዳ እየበዛ ለውጥ እየመጣ አይደለም የሚል መኾኑን ገልጸዋል።

ነባር ችግሮችን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክርን ማቋቋም መቻሉንም አንስተዋል፡፡ በምክክር እና በውይይት ችግሮችን መፍታት አዋጭ እና ጠቃሚ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ምክክሩ ለነገ መሠረት የሚጥል መኾኑን አመላክተዋል፡፡ የትናንቱን ጉዳዮች ለመዝጋት ደግሞ የሽግግር ፍትሕ እንዲኖር እንሥራ፣ ተቋማትን፣ ሕግጋትን እናሻሽል በሚል እየተሠራ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ታግለን ላመጣነው ፍሬ ክብር መስጠጥ ይገባናል ነው ያሉት፡፡ ያገኘነውን የምናመሰግን፣ ለቀረው በጋራ የምንሠራ ከኾነ የምናስበው ለውጥ ይመጣልም ብለዋል፡፡ መንግሥት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መሥራቱን አንስተዋል፡፡ አካታች የፖለቲካ ባሕል መፍጠር የለውጡ ውጤት ነው ብለዋል፡፡ ከጠመንጃ ወደ ጠረጴዛ እንሸጋገር ብሎ ለውጡ መጋበዙንም ገልጸዋል፡፡

ዋልታ ረገጥ አስተሳብ ይቅር በጋራ ኾነን ለሀገር እንሥራ ስንል በብሔር በሽታ ተጠምቆ የሚሠራው ሁሉ በብሔር በሽታ ሊከሰን ይፈልጋል ነው ያሉት፡፡ አዲስ እሳቤን የመቀበል ችግር መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ ታላቅ ለውጥ እያመጣች ያለችን ሀገር በትንሽ ነገር የማጠልሸት ጉዳይ መኖሩንም አንስተዋል። ግጭት እንዳይሸጋገር በምክክር እናቁመው ብለን ጦርነትን ለማቆም ያልከፈልነው ዋጋ የለም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ጦርነት እንዳይጀመር ብዙ ለምነናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስንለምን ደካማ ኾነው ነው ይሉናል፤ ሲቆነጠጡ ደግሞ ጀኖሳይድ ነው ይላሉ፤ መፍትሔው መገዳደልን ማቆም ነው ብለዋል፡፡ ጦርነት መጀመር በጣም ቀላል ነው፤ ጦርነት ማቆም እንኳ ቢሳካ ብዙ ሰው ከበላ በኋላ ነው፤ ውጊያ አንፈልግም ብዙ የልማት ሥራዎች አሉብን፣ ጊዜ የለንም፣ ጊዜ የለንም ማለት ግን ጦርነት አይገባንም ማለት አይደለም ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት አይሳካም፤ እንዳይሳካ አድርገን ተቋማትን ሠርተናል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ጭራሽ አይሳካም፣ ጊዜ አታባክኑ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው፡፡ ዛሬ ሰላም እንዲኾን ነው የምንፈልገው፣ ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁዎች ነን፣ ለምን ከሰላም ውጭ ያለው አማራጭ ዋጋ የለውም ብለዋል፡፡ የጋራ ሀገር ነው፣ አንድ እንሁን፣ በጋራ እናልማ በምርጫ በውይይት እንመን ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።

ከእኔ ብቻ የሚል እሳቤ ይዞ ሥልጣን መያዝ ሀገር ያፈርስ እንደኾነ እንጂ ለውጥ አያመጣም ብለዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያን መውደድ፣ የሥራን ባሕል ማድረግ እና ዜጎችን መደገፍ የተሻለ መኾኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡ የጦርነት ጉዞ አያዋጣም እንወያይ ቢሉ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት ለውይይት ዝግጁ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ግጭት ኢትዮጵያን በእጅጉ እንደሚጎትትም ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ያለው ችግር ዱር የገባ ሥልጣን ይይዛል የሚል ፕሮፓጋንዳ የወለደው መኾኑን አንስተዋል፡፡ ፕሮፓጋንዳውን የሚሠሩት እሳቱ እንደማይነካቸውም ገልጸዋል፡፡ ሊሠሩ የሚችሉ ወጣቶች በመጥፎ ፕሮፓጋንዳ መወሰዳቸውም አመላክተዋል፡፡ ሕዝብ አያምናችሁም የሚለው ጥያቄ እና አመለካከት ሕዝብን መናቅ መኾኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንገድ የሚዘጋውን አምኖ መንገድ የሚሠራለትን አያምንም ማለት ሕዝብን መናቅ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት እስረኛን በመፍታት እና አብረን እንሥራ በማለት እንደማይታማም ገልጸዋል፡፡ በሠለጠነ መንገድ መንግሥት ለመወያየት ዝግጁ ነውም ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቦሩ ሜዳ አንደኛ ደረጃ ትህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ ተመረቀ።
Next article“የፕሪቶሪያው ስምምነት በዋናነት በትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር እንዲቋቋም እና አገልግሎት እንዲቀጥል ማድረግ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)