
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ሥብሠባ እየተካሄደ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ላይ እንዳሉት የውጭ ባንኮችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ውድድርን እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡
ሀገሪቱ ለረዥም ጊዜ ባንኮችን ለውጭ ውድድር ዝግ አድርጋ ስትሠራ መቆየቷን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ግን ውድድርን ለመፍጠር ባንኮችን ለውጩ ዓለም ክፍት ማድረግ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡ ይህን ለማድረግም በባንኮች ላይ መሠራት ያለበት ሥራ ስለመሥራቱ ነው ያስረዱት፡፡ ባንኮችም ጤናማ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኙም አረጋግጠዋል፡፡
የኑሮ ውድነት በዓለም ደረጃም ፈታኝ እንደኾነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓለም ላይ ያሉ ያደጉ ሀገራት ጭምር የኑሮ ውድነቱን ለምርጫ ቅስቀሳ እንደመወዳደሪያ እየተጠቀሙ እንደኾነ ገልጸዋል። ይህም ችግሩ ምን ያክል ስር የሰደደ እንደኾነ ማሳያ ስለመኾኑ አስረድተዋል፡፡ የኑሮ ውድነት በዓለም ላይ ስብራት፣ ጭንቀት እየኾነ ስለመምጣቱ አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያም ከዚህ የተለየ እንደማይኾን ነው የተናገሩት፡፡
ልማትን የሚያፋጥን መንግሥት በዛውም የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ከባድ እንደሚኾንበት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊዚህም ምክንያቱ ለልማት የሚያውለውን ገንዘብ ለኑሮ ውድነት መቀነሻ በድጎማ ስለሚያውለው እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ልማቷን ሳታቋርጥ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ያደረገችው ጥረት የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ምርታማነትን ማሳደግ የሁሉ ነገር ቁልፍ ነው በሚል ሢሠራ ስለመቆየቱም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ስትሠራው የቆየችው የኩታገጠም የስንዴ፣ የሩዝ፣ የፍራፍሬ፣ የጓሮ አትክልት፣ የተማሪዎች ምገባ፣ የማዕድ ማጋራት እና መሰል ሥራዎች ለውጥ ስለማምጣታቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡ ምርት ተመረተ ይባላል ግን ዋጋ አልቀነስም ለሚለው ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያብራሩ የምርት ዕድገት አለ ሲባል ምርትን ሁሉም ቦታ ማዳረስ እና የገበያ ሁኔታውን ማየት ስለሚፈልግ ይህ ሌላ ፈተና እና መሠራት ያለበት ሥራ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ሀገሪቱ በምርት ላይ ውጤት ማስመዝገብ የቻለችው መሬት፣ ውኃ እና የሰው ኀይል ስላላት እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡ የሌማት ትሩፋት ከተጀመረ ሁለት ዓመት ያልሞላው ቢኾንም ያስገኘው ውጤት ግን ተጨባጭ እና ሊታይ የሚችል ስለመኾኑም ነው ያስረዱት፡፡ ባለፈው ዓመት 30 ሺህ የንብ ቀፎ የነበረ ሲኾን በዚህ ዓመት ግን 1 ሚሊዮን የንብ ቀፎ ስለመድረሱ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማር ምርትም በሰባት እጥፍ ስለማደጉ ነው ያብራሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው “በየደረጃው ምርት እና ምርታማነት እያደገ ሲሄድ የኑሮ ውድነቱም እየተሻሻለ እንደሚሄድ” ነው ያብራሩት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!