
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ የተፈሠሩ ሥራዎችን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኾነ የሥራ አጥነት ችግር ነበር፤ አሁንም አለ ብለዋል፡፡ የሥራ አጥነት ቁጥር በየዓመቱ እንደሚጨምር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን ለመቀነስ ተቋም በማቋቋም ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ጥሩ ውጤት መገኘቱንም አስታውቀዋል፡፡ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋልም ብለዋል። 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ የያዙት በሀገር ውስጥ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡
332 ሺህ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ሠልጥነው ወደ ውጭ ለሥራ ተልከዋል ነው ያሉት፡፡ በስታርት አምፕ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡ ዘርፉ በሥፍት ሊሠራበት የሚገባ ተስፋ ሰጪ ነውም ብለዋል፡፡በሀገራቸው ውስጥ ኾነው ከፍተኛ ተከፋይ የሚኾኑበት አጓጊ የሥራ መስክ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ በቀጣይ ጥሩ ሥራ ሊሠራበት እንደሚገባ አመላካች ነገር ነው ሲሉም አክለዋል።
በሌሎች ዘርፎችም የሥራ እድል መፈጠሩንም አመላክተዋል፡፡ የተፈጠረው የሥራ እድል በየትኛውም መመዘኛ አስደናቂ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋሙን የበለጠ በመደገፍ የሥራ እድል ፈጠራን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡ ጤና በተመለከተ ደግሞ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘንድሮው ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል 10 ሚሊዮን ክትባት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
የኩፍኝ ወረርሽኝን ለመከላከልም በ58 ወረዳዎች ክትባት ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡ የወባ አጎበር ስርጭት መከናወኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመድኃኒት አቅርቦትን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ከ8 በመቶ ወደ 36 በመቶ ማደረስ ተችሏል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!