
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ሥብሠባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡
“ኢትዮጵያ የቆመችው በአርሶ አደር፣ ወታደር እና መምህራን ውለታ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን መምህር እና ወታደር ለሀገር ከሚከፍሉት ውለታ ባሻገር የሚከፈላቸው ዋጋ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ነው ያሉት፡፡
በቀጣይ የመምህራንን ሕይወት ለማሻሻል የሚረዱ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ግን ኢትዮጵያ ታመሠግናቸዋለች ነው ያሉት፡፡ የለውጡ መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት አንድም ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በአዲስ አልተከፈተም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያ ማለት ግን ለጥራት የሚያግዙ ማሻሻያዎችን አልሠራንም ማለት ግን አይደለም ብለዋል፡፡
ከስድስት ዓመት በፊት 40 ቢሊዮን ብር የነበረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሁን ላይ 50 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ነው ያሉት፡፡ መንግሥት ለትምህርት ጥራት ትኩረት በመስጠቱ አዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ከመክፈት ይልቅ ጥራታቸውን ማሻሻል እና ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ላይ ትኩረት መደረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!