
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ሥብሠባ እየተካሄደ ነው፡፡
በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ሥብሠባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተገኝተው በምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች ውስጥ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አንዱ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡
ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ጥቅል ምርት በዘርፉ 10 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ማምጣት መቻሉን በማሳያነት አንስተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከ390 በላይ ፋብሪካዎች ማምረት መጀመራቸውን ነው የገለጹት፡፡ በነባር ስሚንቶ ፋብሪካዎች ብቻ 30 በመቶ የምርት ዕድገት መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የለሚ ስሚንቶ ፋብሪካ ብቻ ሥራ ሲጀምር ሀገሪቱ እስከ አሁን የምታመርተውን 50 በመቶ ስሚንቶ የማምረት አቅም እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ ወራትም ሥራ ይጀምራል ብለዋል፡፡
በአምራች ኢንዱስትሪው የታየውን ዕድገት ለማስቀጠል ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለፈ ነጻ የንግድ ቀጣና መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቦታ የማዘጋጀት፣ መሠረተ ልማት የማሟላት እና ባለሃብቶችን የመሳብ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!