
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እንድምታሰገባ ተናግረዋል፡፡ወደብ ሳይኖራት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት አድካሚ ሥራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ግብዓት ብዙ ሃብት፣ ትጋት እና ጉልበት ይፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ባለፈው ዓመት የነበረውን ችግር ለመፍታት በተሠራው ሥራ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ በሥርጭት ላይ ይገኛል፤ ሁለት ሚሊዮን የሚኾው ጅቡቱ እየገባ ነው ብለዋል። ካለፈው ዓመት አንጻር አስደናቂ ሥራ ተሰርቷል፤ ነገር ግን አሁንም ፍጹም ሥራ አይደለም ነው ያሉት፡፡ ምርጥ ዘርን በራስ አቅም ለመሸፈን ሰፊ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡ በመስኖ ልማት ላይም ሠፊ ሥራ መሠራቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 40 ሺህ ፓምፕ መግባቱንም አመላክተዋል፡፡
የመስኖ ግድቦችን ሥራ ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል በርካታ ሀገራት ረድተውናልም ብለዋል፡፡ እነዚህን ሀገራትም አመሥግነዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ እርዳታ የምንፈልገው እህል ሳይኾን ማሽን ሊኾን ይችላል ነው ያሉት፡፡ ውስንነቶችን እየቀነሰን ውጤታማ ለመኾን ጥረት ይደረጋልም ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!