
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዋጋ ንረቱን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 23 በመቶ ዝቀ ማድረግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ.ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኑሮ ውድነት የበርካታ ሀገራት ፈተና ኾኖ ቀጥሏል ብለዋል፡፡ በአንዳንድ ሀገራት ከ60 በመቶ በላይ የደረሰ የዋጋ ንረት እየተመዘገበ መኾኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
በኢትዮጵያም የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ መንግሥት በርካታ ኢንሸቲቮችን ቀርጾ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ የሌማት ትሩፋት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
ምርታማነትን ለማሻሻል እየሠራን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘንድሮው ዓመት ከዓለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ምርት መሰብሰብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም መንግሥት 10 ቢሊዮን ብር ገቢ በመተው መሰረታዊ ሸቀጦችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
የኑሮ ውድነቱ በዜጎቻችን ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለማቃለል እየሠራን ነው ብለዋል። በዚህም የዋጋ ንረቱን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 23 በመቶ ዝቀ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!