
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ12 ሺህ 800 በላይ የባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ.ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ ዘርፉን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት “የፋይናንስ ሴክተሩ በበርካታ አመላካቾች ጤናማ ሂደት ውሰጥ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ12 ሺህ 800 በላይ የባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ዜጎችም የባንክ ደብተር አውጥተው እየተጠቀሙ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይመለስ ብድር አማካኝ አሃዝ 5 በመቶ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ግን 4 ነጥብ 5 በመቶ ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ ይህም ከዓለም አማካኝ ያነሰ መኾኑን ነው የጠቆሙት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ባንኮች ከሚያቀርቡት ብድር ከ80 በመቶ በላይ የግሉ ዘርፍ ተጠቃሚ ነው፤ ይህም የፋይናንስ ዘርፉ በጤናማ እንቅስቃሴ ላይ መኾኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ነገር ግን ባንኮች ከአገር ውስጥ ባለፈ ከዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ከወዲሁ መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!