
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገሪቱን የእዳ ጫና ከሀገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር ወደ 17 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከኢኮኖሚ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ላቀረቡት ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሰጡት ምላሸ፤ የሀገሪቱን የእዳ ጫና ከሀገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር ወደ 17 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
በዓለም ላይ እያጋጠሙ አደጋዎች፣ ወረርሽኞች፣ ጦርነቶች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያጋጠሙ ግጭቶች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሲፈትኑ የነበሩ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ጋር ቢሆን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት በተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መሰረታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ቀውሶች ተቋቁማ እና ያጋጠሙ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር በሁሉም መስኮች አስደማሚ ስኬት ማስመዝገቧን እና ያለባትን የእዳ ጫናን ለማቃለልም ከፍተኛ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ያለብንን የእዳ ጫና ከአገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር ወደ 17 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን አሃዝ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!