
ባሕር ዳር: ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በክረምት እና በተከታታይ ትምህርት መርሐግብሮች በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመርቋል። ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 268 በድህረ ምረቃና 428 ደግሞ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ የሠለጠኑ መኾናቸው ተገልጿል።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በዚህ ዓመት የመውጫ ፈተና ከወሰዱ መደበኛ ተማሪዎች መካከል 83 በመቶ የሚሆኑት ፈተናውን ማለፋቸውን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ የሰላም መደፍረስ፣ የበጀት እጥረት እና የኑሮ ውድነት የመማር ማስተማር ሥራን በከፍተኛ ሁኔታ እንደፈተኑት አንስተዋል። ቢሆንም በዩኒቨርሲቲው መሪዎች እና ሠራተኞች ቁርጠኝነት ተማሪዎችን አስተምሮ ለምረቃ ማብቃቱን ተናግረዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት እና ልምድ በመጠቀም ማኅበረሰቡን በቅንነት ማገልገል እንደሚገባቸውም ፕሬዚዳንቱ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል። ተመራቂ ተማሪዎችም በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት እና ልምድ በመጠቀም ማኅበረሰቡን በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከምስረታው ጀምሮ ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አሠልጥኖ አስመርቋል። በተማረ የሰው ኃይል ግንባታ የበኩሉን ድርሻ ማበርከቱንም ዩኒቨርስቲው አሳውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!