
ጎንደር: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጭልጋ ወረዳ በዘንድሮው ዓመት የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በተመረጡ ሞዴል ተፋሰሶች ላይ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
አሚኮም የችግኝ ዝግጅቱን ለማየት በወረዳው ውስጥ ካሉ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች መካከል አንትራ በተባለው ጣቢያ ተገኝቷል፡፡
በጣቢያው ካሉ ግቢዎች መካከል የቡና ችግኝ ማፍያ ከተዘጋጀበት ተገኝተን ያለውን አጠቃላይ ሥራ ስንቃኝ የጣቢያው ተቆጣጣሪ ቀናው ጠቋሬ ሥራው በጥሩ ሁኔታ ሢሠራ መቆየቱን ነግረውናል፡፡
ተቆጣጣሪው ለዚህ ዓመት የችግኝ ተከላ የችግኝ ማፍላት ሂደት ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ፍል ከማፍላት ጀምሮ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማምረት ረገድ የተለያዩ ተግባራት ሲፈጸሙ መቆየታቸውን እና አሁን ደግሞ ችግኞችን ለተከላ ዝግጁ ማድረጋቸውን ነው የነገሩን፡፡
በጭልጋ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት በተፈጥሮ ሃብት ቡድን የደን ባለሙያ ስጦታው አፍለኝ በወረዳው ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና ለመደበኛ ችግኝ ተከላ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
ችግኝ ከመትከል ባለፈ ተንከባክቦ በማሳደግ ማጽደቅ በዘርፉ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መኾኑን ያነሱት ባለሙያው በወረዳው ከዚህ ቀደም የተተከሉትን ችግኞች በማጽደቅ ረገድ ከ85 በመቶ በላይ መሳካቱን ነግረውናል፡፡
አቶ ስጦታው አርሶ አደሮች ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ሰፊ ትኩረት በመስጠት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ጨምሮ ሌሎች የተመረጡ ችግኞችን በመትከል እና በመንከባከብ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ክትትል እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡
የጭልጋ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደበበ ታከለ ለክረምት የግብርና ሥራዎች ሁሉም ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትን አወንታዊ ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
በተለይ አርሶ አደሮች በአረንጓዴ አሻራ እና በመደበኛ የክረምት ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ብሎም ተገቢውን እንክብካቤ እንዲሰጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በወረዳው የሚተከሉ ችግኞችን በአግባቡ ለማጽደቅ አንድ ብሎክ ለግብርና የሚል እና አርሶ አደሩን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ አሠራር በመቀመር ወደ ተግባር እየተገባ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!