“ክትባት ያልጀመሩ እና ጀምረው ያቋረጡ ሕጻናትን ቤት ለቤት በመሄድ አገልግሎት እየተሰጠ ነው” ጤና ቢሮ

34

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በበርካታ ወረዳ እና ቀበሌዎች ከ5 ዓመት በታች ላሉ ሕጻናት የወረርሽኝ በሽታን መከላከል የሚያስችል የክትባት ዘመቻ እየተካሄደ ነው፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ባታ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ አላምረው የውልሰው የ3 ዓመት ልጃቸውን የሆድ ትላትል መከላከያ ክትባት ሲያሰጡ ነበር ያገኘናቸው፡፡

አቶ አላምረው እንዳሉት ከዚህ በፊት ክትባት በስፋት በማይሰጥበት ጊዜ ሕጻናት ለወረርሽኝ በሽታዎች ተጋላጭ እንደነበሩ እና በዚህም ምክንያት ብዙ ሕጻናት ለህልፈት ይዳረጉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለባለሙያዎችም ቀና ትብብር እንዲኖራቸው እና ልጆቻቸው የክትባት ጊዜያቸው ሳያልፍ በማስከተብ ከበሽታ ሊታደጓቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በዘመቻ ሥራው ላይ ያገኘናቸው የባሕር ዳር ከተማ ሽምብጥ ጤና ጣቢያ ባለሙያ ነርስ ገነት ዓለማየሁ እንዳሉት በቀበሌያቸው በ19 ምድብ የተዋቀረ የዘመቻ ቡድን እንዳለ እና አንዱ ቡድን 872 አባወራ እንደያዘ ተናግረዋል፡፡

“ወደ ሥራው ከገባን ጀምሮ ያገኘናቸው ሕጻናት ባቅራቢያቸው ባሉ የጤና ተቋማት የክትባት ጊዜያቸውን ጠብቀው የተከተቡ በመኾናቸው ሥራችንን አቅልሎልናል” ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል በበርካታ ወረዳ እና ቀበሌዎች ከ5 ዓመት በታች ላሉ ሕጻናት የወረርሽኝ በሽታን መከላከል የሚያስችል የክትባት ዘመቻ እየተካሄደ መኾኑን በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ባለሙያ ጸጋ መኮንን ገልጸዋል፡፡

ዘመቻው ከ731 ሺህ በላይ ክትባት ያልጀመሩ እና ጀምረው ያቋረጡ ሕጻናትን ቤት ለቤት በመሄድ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ እንደኾ ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው ግብዓት ተሟልቶ ወደ ሥራ እንደተገባ እና በክልሉ ጦርነት ባሉባቸው አካባቢዎች ጸጥታውን ታሳቢ ያደረገ ዘመቻ በማካሄድ ሁሉንም ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ያለንን ሃብት ተጠቅመን ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመሥራት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይገባናል” አቶ ወርቁ ሃይለማርያም
Next articleእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ነገ ተማሪዎቹን ያስመርቃል፡፡