
ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ 36ኛ መደበኛ ሥብሠባውን ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ያካሂዳል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 (17) እና በምክር ቤቱ የአሠራር እና የአባላት ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 81 (3) እና አንቀጽ 92 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደበኛ ሥብሠባው ተገኝተው በፌዴራል መንግሥቱ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 (11) እና በምክር ቤቱ የአሠራር እና የአባላት ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 76 መሠረትም ምክር ቤቱ የ2017 የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ አዳምጦ ረቂቅ በጀቱን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በምክር ቤቱ 36ኛ መደበኛ ሥብሠባ ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!