በክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለመቀልበስ እና መንግሥታዊ መዋቅርን ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

11

ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ከልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የጎጃም ቀጣና ያለፉት ሁለት ወራት የሰላም ማስከበር እና የጸጥታ ሥራዎችን በደብረ ማርቆስ ከተማ ገምግሟል፡፡

በምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን እና ደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ስር የሚገኙ የጸጥታ አካላት በተሳተፉበት መድረክ ክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለማሻሻል እና ኅብረተሰቡ ወደ ልማት እንዲያዞር ለማድረግ የጸጥታ ኀይሉ ከኀብረተሰቡ ጋር ኾኖ ሰፊ ርብርብ ስለመደረጉ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡

የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኅላፊ ገደቤ ኃይሉ ክልሉ መጠነ ሰፊ ቀውስ ማስተናገዱን ገልጸዋል፡፡ ይህንን ለመቀልበስ እና እስከ ገጠር ቀበሌ ድረስ መንግሥታዊ መዋቅርን ለመትከል በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የዞኑ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ሙሉ ለማድረግ እና የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ለሰላም እና ጸጥታ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የመድረኩ ተሳታፊ የጸጥታ መሪዎች በሰጡት አስተያየት ውይይቱ የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የታዩ ጠንካራ ሥራዎችን በማስቀጠል እና ክፍተቶችን በመሙላት በቀጣይ ውጤታማ ተግባራትን ለመፈጸም ግብዓት የተገኘበት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ የሰላም ካውንስሉ ያቀረበው የውይይት እና ድርድር ሃሳብ ስኬታማ በማድረግ እና ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ የጸጥታ ኀይሉ በቁርጠኝነት ከማኀበረሰቡ ጋር መሥራት ይገባዋል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በጅቡቲ የዶራሌ ሁለገብ ወደብን ገበኙ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተለያዩ ሹመቶችን ሰጡ።