”የሃይማኖት አባቶች የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም እና አንድነት ለማረጋገጥ የላቀ አስተዋጽኦ አላቸው“ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም

26

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ተጠይቋል፡፡

ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ኀላፊነት እንዲወጡም የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም ጥሪ አቅርበዋል። ‘የሃይማኖት ተቋሞቻችን ለዘላቂ ሰላማችን’ በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በሠላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሚካሄደው የሰላም ኮንፍረንስ ላይ የሁሉም ቤተ እምነት ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም “የሃይማኖት አባቶች የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም እና አንድነት ለማረጋገጥ የላቀ አስተዋጽኦ አላቸው“ ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ ከቂም እና በቀል አስተሳሰብ የወጣ ትውልድ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት አባቶች የተጣለባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል። በተለያዩ ቦታዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች በንግግር እና በውይይት እንዲፈቱ፤ ዜጎች በሰላም እና በነጻነት ወጥተው የሚገቡበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር የሃይማኖት አባቶችን ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።

ሰላም በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መኾኑን ጠቅሰው የሃይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸውን በማስተማር ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ መኾኑንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት። እንደ ኢዜአ ዘገባ ሰላም ከራስ የሚመነጭ እንደኾነ ያነሱት ሚኒስትሩ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በየደረጃው ያሉ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት እና ትብብርን እንደሚሻም ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአግባቡ በመተግበር የክልሉን ኢኮኖሚ ማሳደግ ይገባል” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ
Next articleየገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በጅቡቲ የዶራሌ ሁለገብ ወደብን ገበኙ።