“የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአግባቡ በመተግበር የክልሉን ኢኮኖሚ ማሳደግ ይገባል” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ

58

ደሴ: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ እና በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች የክልል ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች በተገኙበት ክልል አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ተጀምሯል።

በደቡብ ወሎ ዞን በዚህ ክረምት ከ33 ሺህ ሄክታር በላይ በሚኾን መሬት ላይ ከ276 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንደሚተከል እና ከዚህም ውስጥ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኝ እንደሚገኝ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮንን ገልጸዋል። ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደ ክልል ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ አጀበ ስንሻው ተናግረዋል።

ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው እና ለምግብነት የሚውሉ ተክሎች እንደየ አካባቢው ሥነ ምህዳር እየተተከሉ መኾኑንም ምክትል ቢሮ ኅላፊው ገልጸዋል። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ሚዛንን በማስጠበቅ ምቹ እና ተስማሚ አካባቢን ለመፍጠር እንደሚረዳ ነው የገለጹት።

የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአግባቡ በመተግበር የክልሉን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል። በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ 019 ቀበሌ ተገኝተው አረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩት ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ከዚህ በፊት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የለማ እና ፍሬ በመስጠት ላይ የሚገኝን የማንጎ ማሳን ጎብኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ሰልሀዲን ሰይድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓመታዊ የታክስ እና የጉምሩክ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ እንደሚካሄድ የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
Next article”የሃይማኖት አባቶች የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም እና አንድነት ለማረጋገጥ የላቀ አስተዋጽኦ አላቸው“ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም