
አዲስ አበባ: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ዓመታዊ የታክስ እና የጉምሩክ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ማጠቃለያ እና የአዲስ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በዚህ ዓመት በተደረገው ሀገር አቀፍ የግብር ንቅናቄ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማዳረስ የተሠራው ሥራ ውጤታማ እንደነበር የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት የካቲት 23/2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ታውጆ ከተጀመረው የንቅናቄ ሥራ በኋላ በፌዴራል እና በክልል ደረጃ በርካታ ሥራዎች ሢሠሩ እንደነበር ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።
ሚኒስትሯ ሰኔ 27/2016 ዓ.ም ያለፈው ዓመት ንቅናቄ ማጠቃለያ እና የአዲስ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ከቀኑ 7:00 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ገልጸዋል። በመርሐ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች እና ታማኝ ግብር ከፋዮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡- ደረጀ አምባው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!