
ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም ሁሉን ይሰጣል፡፡ ሰላም ሲኖር ዘመድ ከዘመዱ ይጠያየቃል፤ በሬና ገበሬ ይገናኛሉ፡፡ መልካሙን ዘር ወደ ምድር ዘርተው፣ ፍሬውን ይጠብቃሉ፡፡ ነጋዴዎች በሌሊትም ኾነ በቀን ይጓዛሉ፣ አንደኛውን ከሌላኛው ያገናኛሉ፤ ተማሪዎች በማለዳ ተነስተው ወደ ትምህርት ቤት ይገሰግሳሉ፣ በትምህርት ቤትም በጋራ ዘምረው፣ ከሚወዷቸው አስተማሪዎች እውቀትን ይገበያሉ፡፡
ሰላም ሲኖር ማሳው ፆም አያድርም፣ ጎተራው አይጎድልም፣ ገበያው አይራብም፡፡ ሰላም ሲኖር ደም በከንቱ አይፈስስም፣ አጥንትም አይከሰከስም፡፡ ሰላም ሲኖር የንጹሐን ሕይወት አይቀጠፍም፡፡ ሰላም ሲኖር ሕሙማን ወደ ሐኪም ቤት ይጓዛሉ፣ በሐኪም ቤትም ለሕመማቸው ፈውስን አግኝተው ይመለሳሉ፡፡ ሰላም ሲኖር ልጆች ያድጋሉ፣ አረጋውያን ይመርቃሉ፤ ወጣቶች ሀገር ይረከባሉ፣ ለሀገርም ተስፋ ይኾናሉ፡፡ ሰላም በሌለ ጊዜ ግን ቀላል የነበረው ይከብዳል፤ እንደሻ ይገኝ የነበረው ይታጣል፡፡ ሰላም ሲጠፋ ጎተራው ይጎድላል፤ ገበያው ይራባል፤ ጋግሮ መብላት፣ ጠልቆ መጠጣት ይቀራል፡፡
በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት እልፍ ጉዳዮችን አሳጥቷል፡፡ ነዋሪዎች እንደ ወትሮው ሰላም ተሰምቷቸው ከቦታ ቦታ አይንቀሳቀሱም፣ ነጋዴዎች በሰዓቱ ሸቀጥ አያደርሱም፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አይሄዱም፣ ገበሬዎች እንዳሻቸው ግብዓት አይወስዱም፡፡ ከሄዱበት ሳይመለሱ መንገድ የተዘጋባቸው፣ በመናኸሪያ ውስጥ እንዳሉ ትራንስፖርት የቆመባቸው፣ ወደ ሞቀች ቤታቸው መድረሻ አጥተው ችግር የጠበሳቸው ብዙዎች ናቸው፡፡
የወላጆቻቸውን ቀንጃ በሬ ሸጠው በአውሮፕላን የተጓዙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ጭነው መንገድ ሲዘጋ በመንገድ ቆመው ሰንብተው የደፉ ነጋዴዎች፣ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ ከቤታቸው ወጥተው ወደ ቤታቸውም ሳይመለሱ፣ ወደ ቤተሰቦቻቸውም ሳይደርሱ በመካከል የቀሩ ተጓዦች ሞልተዋል፡፡ ወላጆቻቸው ሞተውባቸው አፈር ያላለበሱም ብዙዎች ናቸው፡፡ ወደ ሕክምና ለመሄድ መንገድ ተዘግቶባቸው የቀሩትንም ቤት ይቁጠራቸው።፡፡
አዳነ ምስጋናው ይባላሉ፡፡ ነዋሪነታቸው በዋግኸምራ ብሔሰረብ አሥተዳደር ሰሃላ ወረዳ ነው፡፡ ከሰላም እጦቱ ገፈት ቀማሾች መካከል አንደኛው ናቸው፡፡ ባለቤታቸው ታማባቸው ከሰሃላ ወደ ሰቆጣ ለሕክምና ይሄዳሉ፡፡ የባለቤታቸው የጤንነት ሁኔታ ለተጫማሪ ሕክምና ከሰቆጣ እንደሚያስወጣ እና ወደ ደሴ ሆስፒታል ይሄዱ ዘንድ ግድ እንደሚላቸው ተነገራቸው፡፡ ያን ጊዜ ሲያስታውሱ “ የትራንስፖርት ችግር አለ፤ ባለቤቴ ሪፈር ተብላ ከሰሃላ ወደ ሰቆጣ ሄድኩኝ፡፡ የአምስት ወር ሕጻን ይዛለች፡፡ ከሰቆጣ ወደ ደሴ ለመሔድ ተቸገርን፡፡ አምቡላንስ በነጻ ይሰጠኝ እና ባለቤቴን ደሴ ላድርስ አልኩ፡፡ አርሶ አደርን ነን፣ ምንም የለንም በነጻ ውሰዱልኝ ብለን ብናመለክት የሰማን የለም፡፡ 10 ሺህ ብር ከፍለን በአምቡላን ወደ ደሴ ሄደን፡፡ ወደ ደሴ ስንሔድ መንገድ ላይ የገጠመን ችግር አልነበረም፡፡ ስንመለስ ግን አስቸጋሪ ነበር” ይላሉ፡፡
በደሴ ለቀናት ሲቆዩ በሆስፒታል የሚገኙ አስታማሚዎች ድጋፍ እያደረጉላቸው፤ ከያዙት እያካፈሏቸው፣ እያበረቷቸው መቆየታቸውን ነው የነገሩን፡፡ ችግሩ ግን ከደሴ ወደ ሰቆጣ ሲመለሱ ነበር፡፡ “ ከደሴ ተሳፍረን ስንሄድ ሐይቅ ከተማ ስንደርስ የጸጥታ ችግር አለ ተመለሱ ተባልን፡፡ ተመልሰን፡፡ ወደ ደሴ ለመግባትም አትገቡም ተባልን፡፡ መሀል ላይ ቆምን፣ ከጠዋት 12፡00 ጀምረን እስከ እኩለ ቀን 6፡00 ሰዓት ድረስ ቆምን፡፡ በኋላ ወደ ደሴ መግባት ትችላለችሁ ተባለን፡፡ ደሴ ተመልሰን አደርን፡፡ ተሳፍረንበት የነበረውን መኪና እስከ ሐይቅ ሄጄ ነዳጅ አክስሪያለሁ ብራችሁን አልመልስም አለን፤ ብራችን በዛው ቀረ፡፡ በሌለ ቤታችን ሌላ ትራንስፖርት ቆርጠን መንገዱን ቀይረን በደላንታ አድርገን በጋሸና መሥመር ሄድን፤ የትራንስፖርት ችግር አለ፡፡ ተሰቃይተን ነው የመጣን” ሲሉ አስታወሱ።
የትራንስፖርቱ ችግር እና እንግልቱ ባለቤታቸው ተሰቃይተው እንዲሄዱ እንዳደረጋቸውም ገልጸዋል፡፡ በየመንገዱ ስለሚቆሙ ባሰቡት ቀን ከቤታቸው መድረስ እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ “ መንገድ ላይ ስናድር አልጋ ለመያዝ ብር የለንም፤ መኪና ውስጥም ለመተኛት ሰው ይበዛል አይመችም፡፡ ከደሴ ተነስተን ጋሸና ላይ ውጭ ላይ አደርን፤ ዝናብ አለ፤ ብርድ አለ፤ ነገር ግን አማራጭ ስሌለን አደርን፡፡ በችግር ነው የደረስን” ነው የሚሉት፡፡ ከጋሸና በኋላም ወደ ሰቆጣ ለመሄድ የጸጥታ ችግር አለ ተብለው ቆመው መቆየታቸውንም አንስተዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት ከሚጓዙት ይልቅ መንገድ ላይ የሚቆሙት ይበዛሉ፡፡ በየመንገዱ ይፈተሻሉ፡፡ ዘመድ ባይኖር በሄድነው ቀርተን ነበር ብለዋል፡፡ በራሳችን አቅም አንችልም ነበር ነው ያሉት፡፡ ሆስፒታል መድኃኒት እንደፈለጉ አይገኝም፤ ከውጭ ነው የሚገዛው፣ ይህ ደግሞ ለአርሶ አደር አይቻልም ነው ያሉት፡፡ ይህ ሁሉ ችግር እንዲገጥመን ያደረገው የሰላም እጦት በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡
የሰላም ችግር የፈጠረውን ተጽዕኖ ሲናገሩ “ መናኸሪያ ላይ ከሚሳፈረው ይልቅ የሚለምነው ይበዛል፤ የተቸገረ ሕዝብ ነው ያለው” ሲሉ የታዘቡትንም አካፍለውናል። ሠርተው ለመብላት፣ በሰላምም ለመንቀሳቀስ ሰላም እንዲኾን አጥብቀው እንደሚመኙም ጨመሩልን፡፡ ሰላም እንዲመጣ ጥሩ ማሳብ፣ ለተከፋ ጥሩ ማድረግ፣ መተባበር እና መፋቀር ይገባል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሌጅስቲክስ ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊ ደመላሽ ስንሻው ትራንስፖርት የተረጋጋ ሰላምን ይፈልጋል፤ ሰላም ከሌለ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በጠቅላላው ይቆማል ብለዋል፡፡ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሲቆም የሰዎች እንቅስቃሴ ይቆማል፤ ይህ ሲኾን የሰዎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴ በእጅጉ ይጎዳል ነው ያሉት፡፡ ሰዎች ወደ ሕክምና እንዳይሄዱ፣ ነጋዴዎች ምርት እንዳያዘዋውሩ እንደሚገድባቸውም ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርት ችግር ሕይወትን ምስቅልቅል እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የግብዓት እንቅስቃሴ እንዲቆም እና አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዳያመርቱ፣ አርሶ አደሮችም እንዳያርሱ እንደሚያደርግ ነው ያመላከቱት፡፡ በክልሉ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ትራንስፖርት ለሁሉም አካል አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ለሁሉም አገልግሎት የሚሰጠው ዘርፍ እንዳይደናቀፍ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡ የትራንስፖርት ችግሩ በሚፈጥረው ተጽዕኖ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡ ተጽዕኖው በቀላል ነገር የሚነገር አለመኾኑንም አንስተዋል፡፡ ጊዜ የማይሰጡ ምርቶች እንዲበላሹ እያደረደገ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
የትራንስፖርት መቆራረጥ የማኅበረሰቡን በደስታ እና በሀዘኑ የመገናኘት ልምድ እያስቆመው ነው ብለዋል፡፡ ወላዶች ወደ ሆስፒታል መጥተው ለመታከም እንዲቸገሩ እንዳደረጋቸውም ገልጸዋል፡፡ በመንገድ መዘጋጋት ምክንያት የሚፈጠረው ችግር ጫናው የሚያርፈው ማኅበረሰቡ ላይ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ከታሪፍ እጥፍ እና ከዚያ በላይ እንዲከፍል፣ ተሸከርካሪዎች ከአቅማቸው በላይ እንዲጭኑ እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩም መደበኛ ቁጥጥር ለማድረግ እንደሚያስችግር ነው ያስረዱት።
ለሕዝብ እሠራለሁ የሚል ሁሉ ሕዝብን ከሚጎዳ ነገር መቆጠብ ይገባዋልም ብለዋል፡፡ ትራንስፖርት የሁሉንም ድጋፍ የሚፈልግ መኾኑንም አሳስበዋል፡፡ በክልሉ ሰላም በማምጣት የክልሉን የትራስንፖርት እንቅስቃሴ ወደ መደበኛው መመለስ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ ትራንስፖርት እንዳይቆም ሁሉም አካል ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!