የክልሉን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ ወጣቶች ከሰላም ካውንስሉ ጎን ሊቆሙ እንደሚገባ የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

14

ሰቆጣ: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል የተቋቋመው የሰላም ካውንስል ያቀረበው የሰላም ጥሪ ወቅታዊ መኾኑን የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ተናግረዋል። ወጣት አንባየ መኮነን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ስጋት ኾኗል ብሏል።

ችግሩን ለመፍታትም ሕዝባዊ ውይይቶች መካሄዳቸው መንግሥት እና ሕዝብን ያቀራርባል ነው ያለው። የሰላም ካውንስሉ ያቀረበው ጥሪ ወቅቱን የጠበቀ ነው ያለው ወጣት አንባየ ለተግባራዊነቱ ወጣቶች ከጎናቸው ሊቆሙ ይገባል ብሏል። የሰላም እጦት በማኅበረሰቡ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ያለው ወጣት ምህር ንዋይ ወርቁ በክልሉ ሕዝብ የደረሰውን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ለማካካስ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም ካውንስሉን ጥሪ ሊቀበሉ ይገባል ነው ያለው።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ሔኖክ ነጋሽ ከሰሜኑ ጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንዳልተገኘበት ሁሉ በአማራ ክልል የተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነትም የከበረውን የሰው ሕይወት እየቀጠፈ ነው ብለዋል። መንግሥት ችግሩን ለመፍታት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረቡ ለሰላም ቁርጠኛ መኾኑን እንደሚያሳይም አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ሔኖክ በሕዝባዊ መድረኮች የተመረጡ የአማራ ክልል የሰላም ካውንስሎች ያቀረቡት መግለጫ ሁለንተናዊ ፋይዳው የጎላ እንደኾነም አስረድተዋል። ታጣቂ ኀይሎች በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ያሳሰቡት ኀላፊው የክልሉ ወጣቶች ከሰላም ካውንስሉ ጎን ሊቆሙ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ተፈጥሮና የበለፀገች ሀገር ይገባዋል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ
Next articleየሆቴሎች የኮኮብ ደረጃ ምደባ በአዲስ መልክ እንደሚሠራ የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡