“መደጋገፋችን የቆየ እሴታችን ቢኾንም ይበልጥ በማጎልበት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

49

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ2017 ዓ.ም ክልል አቀፍ የክረምት በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በኮምቦልቻ ከተማ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ከፍተኛ የክልል የሥራ ኀላፊዎቸ ተገኝተዋል። አቶ አረጋ ከበደም በኮምቦልቻ ከተማ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ቤት ሥራ በማስጀመር በይፋ ክልል አቀፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አስጀምረዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በየአካባቢያችን የሚገኙ አቅመ ደካሞችን በመደገፍ እና በተለያዩ በጎ ሥራዎች በመሰማራት የ2016 ዓ.ም የክረምት ወራትን ማሳለፍ እንደሚገባ ገልጸዋል። የሰው እና የተፈጥሮ ግንኙነት የተስማማ ይኾን ዘንድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአረንጓዴ አሻራ ሊሳተፍ ይገባልም ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ክልል አቀፍ የበጎፈቃድ አገልግሎትን በደመቀ ሁኔታ በማስጀመራችሁ በክልሉ መንግሥት ስም ማመስገን እወዳለሁ ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “መደጋገፋችን የቆየ እሴታችን ቢኾንም ይበልጥ በማጎልበት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል” ብለዋል። የክረምት በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ፤ የአረጋውያንን ቤት በመጠገን፤ በችግኝ ተከላ እና የጎዳና ላይ ሩጫ በማከናወን፣ ለአቅመ ደካሞች ማዕድ በማጋራት፣ ለአካል ጉዳተኞች የዊልቸር ድጋፍ በማድረግ እና የደም ልገሳ በማከናወን ተካሂዷል።

እንደ ክልል ከ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በክረምት በጎ ፈቃድ ሥራው ላይ ተሳትፎ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ ወጣት እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ዒሳ ተናግረዋል። የዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከወትሮው ለየት የሚያደርገው በወጣቶች መሪነት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፍቃድ ሥራው ላይ መሳተፋቸው ነው ተብሏል።

13 ሚሊዮን የሚኾን የኅብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ያነሱት ቢሮ ኀላፊው በገንዘብ ሲተመንም 6 ቢሊዮን ብር የሚገመት አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ወጣቶች በችግኝ ተከላ፤ በደም ልገሳ፤ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን፣ መዓድ በማጋራት፣ በክረምት ትምህርት፣ በተለያዩ የጤና እና የግብርና ሥራዎች ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ታውቋል።

ይህንን ሁሉ ተግባር ለማከናወን ከሁሉ በላይ ሰላም ወሳኝ በመኾኑ በተለይ ወጣቶች የሰላም አምባሳደር መኾን እንደሚገባቸው አቶ እርዚቅ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- መስዑድ ጀማል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕል ማዕከሉ ግንባታ ጉዳይ!?
Next article“ቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ተፈጥሮና የበለፀገች ሀገር ይገባዋል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ