የባሕል ማዕከሉ ግንባታ ጉዳይ!?

31

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕል ማዕከላት የአንድን ማኅበረሰብ ባሕል፣ ታሪክ እና ወግ በአንድ ቦታ በማዕከል ለማስተዋወቅ እና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ያገለግላሉ፤ ሥልጠና እና ምርምሮችን ለማከናወን፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን ጭምር በማምረት ለገበያ በማቅረብ ባሕልን የገቢ ምንጭ ለማድረግም ጭምር ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

በአማራ ክልልም የክልሉን ባሕል፣ ታሪክ፣ ወግ እና እሴቶችን የሚወክሉ የባሕል ማዕከላት ግንባታ በተለያዩ አካባቢዎች ከተጀመሩ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ የጎጃም ባሕል ማዕከል እና አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክት አንዱ ነው። የፕሮጀክቱ ኀላፊ ሰሎሞን አባተ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ግንባታው በ2012 ዓ.ም ውለታ ተይዞለት ነበር። በ2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ቢታሰብም አሁን ላይ ሥራው 53 በመቶ ላይ ይገኛል።

የስሚንቶ አቅርቦት ችግር ለግንባታው መጓተት ዋነኛ ምክንያት ኾኖ ተቀምጧል። ግንባታው የተለየ ቴክኖሎጅን የሚጠቀም በመኾኑ ግብዓቶችን በቀላሉ ማግኘት አለመቻሉም ሌላው ችግር ነው ብለዋል። የግንባታ እቃዎች የዋጋ ንረት እና በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ተንቀሳቅሶ አለመሥራት ሌሎች ምክንያቶች ተደርገው ተቀምጠዋል።

አሁን ላይ የተፈለገው ግብዓት በተፈለገው ቦታ አለማግኘት፣ ገበያ ላይ የተገኘውን ግብዓት ደግሞ ለማቅረብ ችግር መኖሩንም ገልጸዋል። ግንባታውን በ2017 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ በዕቅድ መቀመጡንም ገልጸዋል። የምሥራቅ ጎጃም አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ የባሕል ማዕከል እና አዳራሽ ግንባታ ሥራው አጠቃላይ የጎጃምን ባሕል፣ ወግ እና ታሪክ በአንድ ማዕከል በማደራጀት ለማበልጸግ፣ ለመዘከር እና የጥናት እና ምርምር ማዕከል ለማድረግ ያስችላል። የጸጥታ ችግሩ በግንባታ ሂደቱ ላይ መጓተት መፍጠሩን ያነሱት አሥተዳዳሪው አሁን ላይ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም መሻሻል አሳይቷል።

ግንባታው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ዞኑ ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት። የጎጃም ባሕል ማዕከል አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክት የተለያዩ ክፍሎች አሉት። 1 ሺህ 343 ወንበሮች ያሉት የሥብሠባ አዳራሽ፣ 500 ወንበሮች ያሉት ሁለት ሲኒማ አዳራሾች፣ የተለያዩ ቢሮዎች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያ፣ ባር፣ ካፍቴሪያ፣ ሬስቶራንት፣ ሲኒማ፣ ሱቆችን እና መሰል ነገሮችን ያካተተ ነው። ፕሮጀክቱ አራት ባለ ሁለት እና ባለ አራት ወለል የያዘ ሲኾን ከ359 ሚሊዮን 743 ሺህ ብር በላይ በጀት ተመድቦለታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበግጭትቶች ምክንያት ለተጎዱ ሴቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።
Next article“መደጋገፋችን የቆየ እሴታችን ቢኾንም ይበልጥ በማጎልበት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ