በግጭትቶች ምክንያት ለተጎዱ ሴቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።

20

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በኢትዮጵያ ከግጭት ጋር በተያያዘ ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች የሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ ተደራሽ እንዲኾን የክትትል ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ከተመድ ዋና ጸሐፊ የሥርዓተ ጾታ ጉዳይ ኀላፊ ክርስቲያን ኤፍ ሰንደርስ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ዶክተር ኤርጎጌ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን እና ትንኮሳዎችን ለመከላከል የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እና ሴቶችን ለማብቃት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ ያለዕድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት በመቻሉ አበረታች ውጤት መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሽልማት መብቃቷን እና ለተገኘው ስኬትም የዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ በግጭት እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች ለመደገፍ እና ለማቋቋም መንግሥት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑን አስረድተዋል፡፡

የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል የዓለም አቀፍ ተቋማት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ ማቅረባቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡ ክርስቲያን ኤፍ ሰንደርስ ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከል እና መብታቸውን ለማስከበር እንዲሁም ከግጭት ጋር በተያያዘ ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ ተደራሽ እንዲኾን በቅንጅት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ተመድ የክትትል ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው ነው የገለጹት፡፡ በቀጣይም ሚኒስቴሩ ለሚሠራቸው ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾናቸውን ኀላፊው አስታውቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ያሠለጠናቸውን 5 መቶ 44 ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ አስመረቀ።
Next articleየባሕል ማዕከሉ ግንባታ ጉዳይ!?