
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የሴኔት አባላት፣ የተመራቂ ወላጆች፣ የአካባቢው ታላላቅ የሀገር ሽማግሌዎችና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በተገኙበት በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች ያሠለጠናቸውን 5 መቶ 44 የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ ተማራዎችን አስመርቋል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶ.ር) በመልእክታቸው “በጉዟቹህ ያጋጠማችሁ ውጣ ውረድ ስፍር ቁጥር ከሌለው የጥናት ጊዜያት በኋላ ለዚህ የደስታቹህ ቀን በመድረሳቹህ እንኳን ደስ አላችሁ፤ ምንም እንኳን ከፊታቹህ የበለጠ ፈተናዎችና ሥራዎች ቢኖሩም ለዚች ቀን በመድረሳቹህ ግን ልትኮሩ ይገባችኋል” ብለዋል።
አዲስ ሁኔታ ሲገጥማችሁ ስለምንነቱ አስተውላቹህ እዩ፣ በደንብ አድምጡ፣ ይበልጥ ደግሞ በጥሞና አስቡ፣ አዲስነቱን ተረድታችሁ የማታውቁት መሆኑን ከተገነዘባችሁ በኋላ በንፁሕ ህሊና በሚዛናዊነት ስትፈትሹት ባለማወቅ ከመሳሳት ትቆጠባላችሁ፤ አዲሱን ሁኔታ በሚመጥን አዲስ ብልሃት ብቁ ሆናችሁ ትገኛላችሁ ያሉት ዶክተር አነጋግረኝ አዲስ ሁኔታን በአዲስነቱ ማስተዋል በማናውቀው ብዙ ነገር እንደሚያስተምር መክረው በድጋሜ የእንኳን ደስ አላችሁ ምኞታቸውን ገልፀዋል።
በመጨረሻም በየትምህርት ክፍሉና ከአጠቃላይ ተራቂዎች መካከል የላቀ ውጤታ ላስመዘገቡ የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂዎች የእውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። 3 ነጥብ 94 ውጤት በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው በጤና ትምህርት ክፍል የሜዲካል ላብራቶሪ ተማሪ ደሳለኝ አሻግሬ ለከፍተኛ ውጤት የበቃው ጊዜዉን በአግባቡ ተጠቅሞ በማጥናቱ መሆኑን ተናግሯል።
በተሰማሩበት የሥራ መስክ ስኬታማ ለመሆን ከፍተኛ ትዕግስትና ፅናት ይጠይቃል ያለው ተመራቂ ደሳለኝ ጊዜዬን በአግባቡ በመጠቀሜ በከፍተኛ ማዕረግ ለመመረቅ ችያለሁ ብሏል። የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ተማሪ ተመራቂዋ ተማሪ አመለወርቅ ቢራራ 3 ነጥብ 71 ውጤት በማምጣተ በከፍተኛ ማዕረግ መመረቋንና ለከፍተኛ ውጤት ያበቃት በፕሮግራም በማጥናቷ መሆኑን ተናግራለች።
ተመራቂዎች ሀገርራቸውንና ወገናቸውን በታማኝነት ለማገልገል ቃል ገብተዋል። አሚኮ ከደቡብ ጎንደር ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ተማሪዎቹን ያስመረቀው ለ11ኛ ጊዜ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!