የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በሚል የቀረቡለትን 12 ጉዳዮች መርምሮ አጸደቀ።

35

ባሕር ዳር: ሰኔ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

በጉባኤው የሕገ መንግሥት ትርጉም እና የውሳኔ አፈጻጸም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል እና የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል በሕገ መንግሥት ትርጉም እና የውሳኔ አፈጻጻም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ በኩል ቀርቦ ምክር ቤቱ በጥልቀት መርምሯል።

የሕገመንግሥት ትርጉም እና የውሳኔ አፈጻጸም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በሚል ያቀረባቸውን 12 ጉዳዮች በመመርመር ስምንቱን ጉዳዮች የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል፣ አራቱን ጉዳዮች ደግሞ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በማለት ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል። ምክር ቤቱም የቀረቡለትን ጉዳዮች በጥልቀት መርምሯል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ምክር ቤቱ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እና የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እንዲከበሩ በርካት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። በቋሚ ኮሚቴው የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ እንዲፀድቅ ለድምጽ ያቀረቡ ሲኾን ምክር ቤቱም በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

ቋሚ ኮሚቴው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል በተሰጣቸው ውሳኔዎች ቅር በመሰኘት ለምክር ቤቱ በይግባኝ የቀረቡ 117 ጉዳዮችን አስመልክቶ ቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርቧል።

ምክር ቤቱም በቋሚ ኮሚቴው የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ አፈ ጉባኤው ድምጽ እንዲሰጥባቸው ባቀረቡት መሠረት ምክር ቤቱ 115ቱን ጉዳዮች የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም እንዲሁም ሁለት ጉዳዮች ደግሞ በቋሚ ኮሚቴው የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል የተባለው እንዲፀድቅ በሙሉ ድምጽ በመቀበል አጽድቋል።

በመጨረሻም የተጓደሉ የቋሚ ኮሚቴ አባላትን በመተካት ምክር ቤቱ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን መደበኛ ጉባኤ ማጠናቀቁን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ1 ሚሊዮን በላይ ሕጻናትን ለመከተብ የ10 ቀናት ዘመቻ ይፋ ተደረገ።
Next article“በገበያ ተኮር ምርቶች ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል” የምዕራብ ጎንደር ዞን