
አዲስ አበባ: ሰኔ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዜጎች ከጥላቻ እና መገዳደል ወጥተው ወደ መግባባት እንዲመጡ ሚዲያዎች ኀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም አሳሰቡ።
“ሚዲያዎቻችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ መልዕክት ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው። የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም በሀገር ዘላቂ ሰላም እና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ሚዲያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል። ሚኒሰትሩ ሚዲያ ለሕዝብ የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ሀገራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ በጥንቃቄ መምራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ የሁሉም ነገር መሠረት የኾነውን ሰላም ለመጠበቅ እንደ ሀገር ያሉ የጋራ ፍላጎት እና ልዩነቶች ላይ ሚዲያ በበቂ ሁኔታ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል። የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የሚዲያ አካላት የተሳተፉበት ኮንፈረንስ ላይ “ሚዲያ እና ሰላም በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ” በሚል ርዕስ መነሻ ጹሑፍም ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!