በትምህርት ላይ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

12

ባሕር ዳር: ሰኔ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከጎንደር ቀጠና የትምህርት መሪዎች ጋር በመተባበር “ትምህርት ለትውልድ” የንቅናቄ መድረክ አዘጋጅቷል።

በንቅናቄ መድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ጌታቸው ቢያዝን ከትምህርት ተሳትፎ አኳያ በክልሉ እስካሁን በነበረው ሂደት የተገኙ ውጤቶች እንዳሉ ሁሉ የአሠራር ክፍተቶች መኖራቸውንም አንስተዋል። በተለያዩ ጊዜያት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በትምህርት ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድረዋል ብለዋል። በዚህም የአንደኛ፣ መካከለኛ እና የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ተሳትፎ ቀደም ሲል ከነበረው እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል።

ድህነትን እና ኋላቀርነትን ማስቀረት የሚቻለው የትምህርት ተሳትፎን እና ጥራትን በማሳደግ እንደኾነ የገለጹት አቶ ጌታቸው ቢያዝን በትምህርት አፈጻጸሙ ላይ እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። ለዚህ ደግሞ የ2017 ትምህርትን ለመጀመር ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት የሚገኝ ሲኾን የሰሜን፣ የምዕራብ እና የማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞኖች እና የጎንደር ከተማ የትምህርት መሪዎች መሳተፉቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክልሉ 678 ሚሊዮን ብር ለሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተዘዋዋሪ ብድር ተመቻችቷል” ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር)
Next articleየብዙኀን መገናኛ ተቋማት ለሕዝብ የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ሀገራዊ መግባባት ላይ ሊሰሩ ይገባል ተባለ።