ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ።

30

ባሕር ዳር: ሰኔ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቱርኪዬ መንግሥት አመቻቺነት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተደረገውን ውይይት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የሁለቱ ሚኒስትሮች ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል ላሉ አለመግባባቶች መፍትሄ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ግልፅ እና ወዳጅነት የተሞላበት የሃሳብ ልውውጥ የተደረገበት እንደነበር ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።

በቱርኪዬ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊዳን ጋባዥነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እና የሶማሊያ ፌዴራል ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂ ሰኔ 24/2016 ዓ.ም በአንካራ ተገናኝተው መወያየታቸውን ነው የገለጸው።

በቱርኪዬ መንግሥት አመቻቺነት የተካሄደው የሁለቱ ሚኒስትሮች ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል ላሉ አለመግባባቶች መፍትሄ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ግልፅ እና ወዳጅነት የተሞላበት የሃሳብ ልውውጥ የተደረገበት እንደነበር በመግለጫው ተመላክቷል። ሁለቱ ሚኒስትሮች ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል። የቱርኪዬ መንግሥት ውይይቱን ለማመቻቸት ስለተጫወተው ገንቢ ሚናም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች መልካም ጉርብትናን እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ከግምት በማስገባት መፍትሄዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክክሮችን ለመቀጠልም መስማማታቸው ተገልጿል። ሁለቱ ሚኒስትሮች የቱርኪዬ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ምክክሩን ለማስተናገድ የወሰዱትን ተነሳሽነት በማድነቅ ሁለተኛ ዙር ውይይታቸውን ነሐሴ 27/ 2016 ዓ.ም በአንካራ ለመቀጠል መስማማታቸውም ተመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የሸዋ ቀጣና የሁለት ወራት የመስክ ስምሪት የአፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
Next article“በክልሉ 678 ሚሊዮን ብር ለሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተዘዋዋሪ ብድር ተመቻችቷል” ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር)