
ባሕር ዳር: ሰኔ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ደም በመለገስ እና በተዛማጅ ሰብዓዊ አገልግሎቶች ላበረከተው አስተዋጽኦ ተመስግኗል። በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የባሕር ዳር ደም እና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት 20ኛውን የደም ልገሳ ቀን ሲያከብር ደም ለጋሾችን አመሥግኗል። በደም ልገሳ እና ተዛማጅ አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና እና ምሥጋና የመስጠት መርሐግብር ተከናውኗል።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም ሠራተኞቹ በየጊዜው ደም እንዲለግሱ በማድረግ እና ማኅበረሰቡ ደም በመለገስ ሕይወትን እንዲታደግ በዘገባም ብዙ ሥራ ሰርቷል። ለዚህም እውቅና እና ምስጋና ተችሮታል። ጋዜጠኛ ሺመልስ ከበደ በጎ ተግባርን እና ሰብዓዊነትን ከቤተ ክርስቲያን እንደተማሩት ይናገራሉ። ”መልካም ሥራ ለራስ ነው፤ የልብ እርካታ አለው፣ በፈጣሪ ዘንድም ዋጋ አለው” ያሉት ጋዜጠኛ ሺመልስ የበጎ አድራጎት ሥራን በወጣትነታቸው ጊዜ እንደጀመሩ ገልጸዋል።
ለሌላው አርዓያ መኾን መልካምነትን ማሳየት እንደኾነ ተረድቼ በአሚኮ ደም መለገስን ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በማሥተባበር ላይ እገኛለሁ ሲሉ ገልጸዋል። ለ21ኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ያነሱት ጋዜጠኛው የጤና እክል አጋጥሟቸው እንኳ የማሥተባበር ሥራቸውን እንዳላቀሙ ያስታውሳሉ። ደም መለገስን ጨምሮ በጎ ሥራን ወጣቶች እንዲለምዱ እየሠሩ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት።
የባሕር ዳር ደም እና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጋዜጠኛ ሽመልስ ከበደን ሕይወት ለማትረፍ ላበረከቱት የሰብዓዊነት ሥራ የምስክር ወረቀት በመስጠት አመሥግኗቸዋል። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዪኒኬሽን ዳይሬክተር መሠረት አስማረ አሚኮ ከዘገባ ሥራዎች በተጓዳኝ ለበጎ አድራጎት ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ችግረኞችን መርዳት፣ በዓመት በዓል መጠየቅ፣ ከደም ልገሳ ጋር የተያያዙ ዘገባዎችን በሁሉም ሚዲየሞች በነጻ መሥራት እና ሠራተኞቹን አሥተባብሮ ደም መለገስ ተጠቃሾች መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ቀይ መስቀል ደም በሚያሠባሥብበት ወቅት ደም ለለገሱ ሰዎች የፈሳሽ መተኪያ ሚሪንዳ እጥረት ገጥሞ አሚኮ የሸፈነበትን ጊዜም ያስታውሳሉ።
አሚኮ የደም ልገሳ ሥራን ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በትኩረት እየሠራ እንደቆየ የገለጹት አቶ መሠረት ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ ደግሞ በየሦስት ወሩ ደም መለገስን በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል። ለደም ልገሳ አስተዋጽኦ ዕውቅና ስለተሰጠን እናመሠግናለን ያሉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዪኒኬሽን ዳይሬክተሩ የደም ልገሳ እና ሌሎች የሰብዓዊ አገልግሎት ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለንም ብለዋል።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የባሕር ዳር ደም እና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ደም ለጋሾችን ባመሠገነበት መድረክ ከአሚኮን በተጨማሪ ግለሰቦችን ደም በመለገስ የሰው ሕይወትን ለመታደግ ለዋሉት ውለታ ዕውቅና በመስጠት አመሠግኗቸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!