
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ 6ኛ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተዘጋጀው የመትከያ ቦታ የአፕልና የደጋ ቡና ችግኝ በመትከል ተጀምሯል፡፡ መርሐ-ግብሩን ያስጀመሩት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) “ግብርናና አረንጓዴ ልማትን ስናካሂድ የነበረው ራቅ ወዳሉ አካባቢዎችና ወደ ወረዳዎች በመሄድ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላን ከግቢያችን ጀምረናል” ብለዋል።
ፕሬዘዳንቱ ግብርናና አረንጓዴ ልማት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የትኩረት መስክ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ “የኢትዮጵያ፣ የክልላችን ብሎም የአካባቢያችን የኑሮ መሰረት ግብርና በመሆኑ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ምርምሩን፣ የማኅበረሰብ አገልግሎቱንና የቴክኖሎጅ ሽግግሩን አብረን ማስኬድ አለብን” ያሉት ፕሬዘዳንቱ ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ ግብርናና አረንጓዴ ልማትን እያሰፋና እየሠራ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!