
ባሕር ዳር: ሰኔ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የካቲት 17/2016 ዓ.ም ባስተላለፈው ዘገባ ባሕር ዳር ከተማ ውሰጥ ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ መኾኑን መቃኘቱ ይታወሳል። “ቅርብ ወራጅ 10 ብር” በሚል ርእስ ባስነበበው የትዝብት አምዱ በተለይ ታክሲዎች በትራንስፖርት ታሪፉ መሠረት እንደማይጭኑ ምልከታውን አሳይቷል። ተሽከርካሪዎች መጫን ከሚችሉት በላይ ተሳፋሪን እየጫኑ መኾኑንም አስነብቦ ነበር።
ከአራት ወራት በኋላ የትራፊክ እንቅስቃሴው ያለበትን ሁኔታ ለመታዘብ ወደ ከተማው የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰናል። በቅኝታችንም ታክሲዎች በትክክለኛው ታሪፍ እንደማይጭኑ ተመልክተናል። ተሽከርካሪዎች መጫን ከተፈቀደላቸው ተሳፋሪ በላይ ፍፁም ከሥርዓት ውጭ እንደሚጭኑም ታዝበናል። የትራፊክ ፖሊሶቸ ቁጥጥር ወጥነት የጎደለው በመኾኑ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን በተሟላ መንገድ ወደ ሥርዓት ማስገባት እንዳልተቻለ አስተውለናል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት መምሪያ የመንገድ ትራፊክ ቡድን መሪ አበበ ብርሃኔ በከተማዋ የትራፊክ እንቅስቃሴ ዙሪያ አሚኮ ያስተዋላቸውን ችግሮች ይጋራሉ። ችግሩን ለማስተካከል ከትራፊክ፣ ከትራንስፖርት ማኀበራት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደኾነ ይገልጻሉ።
ትርፍ የሚጭኑ፣ ከታሪፍ በላይ የሚቀበሉ፣ አጭር መንገድ አንጭንም የሚሉ የትራንስፓርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ክትትል በማድረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ስላማዊ እና ጤናማ ለማድረግ እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል። የትራፊክ ሕግን በማስከበሩ ሂደት የተጠቃሚው ማኀበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መኾኑን ያነሱት ቡድን መሪው ማኅበረሰቡ ግን ትራፊኮችን እያገዘ እንዳልኾነ ነው የገለጹት።
አንዳንድ ጊዜ ማኅበረሰቡ አጥፊዎች እንዳይቀጡ ተባባሪ የመኾን አዝማሚያም ይታያል ብለዋል። ሕግ የጣሰ አሽከርካሪ ሲያዝ ተሳፋሪዎች በእኛ ገንዘብ ምን አገባችሁ፣ እንቸኩላለን እንሂድበት፣ እኛ መጉላላት እየደረሰብን ነው የሚሉ እና ሌሎች ወቀሳዎችን እያስተናገድን ነው ብለዋል አቶ አበበ። በተለይ ማኅበረሰቡ መረጃን ይዞ፣ ሰሌዳ መዝግቦ እና ክሶችን አደራጅቶ ሲመጣ እኛ እንቀጣለን፤ ለዚህም ሙሉ እርግጠኛ ነን ብለዋል።
የትራፊክ እንቅስቃሴው ጤናማ አለመኾን የሚጎዳው ተጠቃሚውን በመኾኑ ማኅበረሰቡ ለሕግ መከበር ከምን አገባኝ ስሜት ወጥቶ በባለቤትነት ስሜት መተባበር አለበት ብለዋል። በመጨረሻም ማኀበረሰቡ ትራንስፖርት ላይ ችግሮችን ሲያስተውል ሥራ ላይ ለሚገኙ ትራፊኮች እና ተቆጣጣሪዎች መረጃ መስጠት እንደሚችል አስገንዝበዋል። በተጨማሪም በስልክ ቁጥር 0583205744 ላይ በመደወል መረጃ መስጠት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!