
ባሕር ዳር: ሰኔ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገራችን የተለያዩ ቦታዎች የክረምቱን መግባት ተከትሎ የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመር በመምጣቱ ይነገራል። የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እና ለመቆጣጠር እንዲቻል ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ድንገተኛ የጤና አደጋ ስጋት ምላሽ ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው ተብሏል፡፡
በተቀናጀ የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራዎች ዙሪያ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ከክልል ጤና ቢሮ ኀላፊዎች ጋር በበይነ መረብ የታገዘ ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱ ላይም ሁሉም የክልል ጤና ቢሮ ኀላፊዎች የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራዎች ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አቅርበው ተገምግሟል። የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራዎችን በበላይነት የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች በትኩረት እየተከታተሉት እና እየመሩት መኾኑ ተመላክቷል፡፡
በተለይ በዘመቻ የሚከናወኑ ተግባራትን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ያነሱት ሚኒስትር ድኤታው ከክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ጋር ማቀናጀት እንደሚገባም ጠቁመዋል። የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ማኅበረሰቡን ማሳተፍ እና ማስተሳሰር እንደሚገባ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ተናግረዋል፡፡
የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የግብዓት አቅርቦትን አስመልክቶ የስርጭት ሰንሰለቱ ላይ የሚስተዋሉ መቆራረጦችን አስመልክቶ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም በትብብር መሥራት እንደሚገባ ተነስቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በ165 ወረዳዎች ላይ የቤት ውስጥ የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት እየተደረገ ነው ያሉት ዶክተር ደረጀ የርጭት ሥራውን ወደ ቀሪ ወረዳዎች በማዳረስ የመከላከሉን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ከአጎበር ስርጭት ጋር በተያያዘም በበጀት ዓመቱ በርካታ የአጎበር ሥርጭት ተካሂዷል ያሉት ሚኒስትር ድኤታው ከአጠቃቀም አንጻር ያሉ ውስንነቶች ላይ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባልም ብለዋል። በቀጣይም የተጀመሩ መልካም ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተጠቁሟል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!