የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎችን ሕግንና የዜጎችን ዘላቂ አብሮነት መሰረት ባደረገ መልኩ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።

76

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ጊዜው የ1ኛ መደበኛ ጉባኤ ቃለ-ጉባኤን በማጽደቅ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

በጉባኤው የምክር ቤቱ አባላት የ2016 በጀት ዓመት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴና የማንነት አስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርቶች ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ሕግና አሠራርን ብሎም የዜጎችን ዘላቂ አብሮነት መሰረት ባደረገ መልኩ ምላሽ ለመስጠት ምክር ቤቱ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ የፌደራል መንግሥትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክልሎች ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ጨምሮ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢና የደቡብ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ የተነሳበትን ገፊ ምክንያት መነሻ በማድረግ ሌላ ጥያቄ በማያስነሳ መልኩ ምላሽ ለመስጠት በጥንቃቄ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ለዚህም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመከተል ሊሳተፉ የሚገባቸውን ወሳኝ አካላት በማሳተፍ መፍትሔ ለመስጠት እየተሠራ ስለመሆኑም እንዲሁ።

የማንነት፣ አስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ጸኃፊ ፍቅሬ አማን፤ በደቡብና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች የቀረቡ የማንነት አቤቱታና ይታወቅልኝ ጥያቄዎችን በዘላቂነት መፍትሔ መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ባሕል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ዕውቀትና ልምድ ሰንዶ ለማስተላለፍ የማንነት መገለጫ አትላስ (ፕሮፋይል) ማደራጀት የሚያስችል ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሌሎች የማንነት ይታወቅልኝና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች ውሳኔ ለመስጠት የሚያስፈልግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም ምክር ቤቱ ለማንነትና አስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያለውን ተቋማዊ ዝግጁነት አድንቀዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመትም የሕዝቦችን ዘላቂ አብሮነት ታሳቢ በማድረግ ለማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አንስተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ የፌዴራል መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ በዝርዝር ይወያያል።
Next articleበክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ትኩረት እንዲሰጥ ጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።