“የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች በሀገር ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እድል ይፈጥራል” አቶ ብናልፍ አንዱዓለም

24

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች ከበጎ ሥራዎች ባለፈ በሀገር ግንባታ ሥራ ላይም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት መሆኑን የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱአለም ገለጹ።

የዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል መጀመሩ ይታወሳል።

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱአለም እና የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ መርኃ ግብር በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተካሄደ ያለውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በዚህም የአረጋውያን ቤት እድሳት፣ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ዝግጅትና የችግኝ ተከላ ሥራዎች ተጎብኝተዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱአለም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በመርኃ ግብሩ 20 ሺህ የሚደርሱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች እየተሳተፉ ነው።

መርኃ ግብሩ ተማሪዎቹ አብሮነታቸውንና ሀገራዊ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የበጎ ፈቃድ ሥራው ተማሪዎቹ እርስ በእርሳቸው እንዲተዋወቁ እድል የሚከፍትላቸው መሆኑን ጠቅሰው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች ከበጎ ሥራዎች ባለፈ በአገር ግንባታ ሥራ ላይም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በሀገራቸው መጻኢ እድል በጋራ ከመምከር በተጨማሪ በውይይትና በንግግር አገርን ለመገንባት በሚቻልበት መስክ ላይም የሚወያዩበት መሆኑን ተናግረዋል።

ተማሪ ሚደቅሳ ታደሰ የበጎ ፈቃድ ሥራ ያለማንም ቀስቃሽ የሚሰራና በምትኩም ምላሽ የማይጠበቅበት የሕሊና እረፍት የሚሰጥ ተግባር መሆኑን ይናገራል።

ለዚህም የወጣቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ሊያገለግሉ እንደሚገባ ተናግሯል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ መዝሙረዳዊት ፈለቀ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሀገር ጠቃሚና የህሊና እርካታን የሚሰጥ ተግባር መሆኑን ገልጻለች።

ኢዜአ እንደዘገበው ሌሎች ወጣቶች ከዚሁ የበጎ ፈቃድ ሥራ ተሞክሮ በመውሰድ በራስ ተነሳሽነት ማገልገል እንደሚገባቸው ተናግራለች።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጋምቤላ ክልል የሚገኘውን የአኮቦ ኢትኖ የማዕድን ኩባንያ ጎበኙ፡፡
Next articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ የፌዴራል መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ በዝርዝር ይወያያል።